(መሠረት ሚድያ)- በደሴ ቦሩ ሜዳ ሆስፒታል የሚሰሩ የጤና ባለሙያዎች በዛሬው እለት እያሰሙት ከነበረው የመብት ጥያቄ ጋር በተያያዘ የፀጥታ ሀይሎች ከስራቸው ላይ በማስነሳት ከነ ደንብ ልብሳቸው (ጋውናቸው) በመኪና ጭነው እንደወሰዷቸው ታውቋል።
የጤና ባለሙያዎቹ ወደ 5ኛ ፖሊስ ጣብያ እንደተወሰዱ የታወቀ ሲሆን ከእስሩ በፊት "እየራበን እንድንሰራ አንገደድም" በሚል ግቢ ውስጥ ላማዊ የሆነ ሰልፍ አርገው ወደ ስራቸው እንደተመለሱ ታውቋል።
ይሁንና ወዲያው የፀጥታ አካላት በበርካታ ተሽከርካሪዎች ወደ ጤና ተቋሙ በመግባት ከ10 በላይ የጤና ባለሙያዎችን ይዘው እንደሄዱ ጉዳዩን ከሚከታተሉት ገፆች አንዱ 'Dr. Debol' ፅፎ ተመልክተናል።
ከቀናት በፊት የኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት አቶ ዮናታን ዳኛው እንዲሁም ሦስት የአርባ ምንጭ ጠቅላላ ሆስፒታል ዶክተሮች በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወቃል።
የጤና ባለመያዎቹ የሰጡት ቀነ-ገደብ አንድ ቀን የቀረው ሲሆን 'የመጨረሻውን ምዕራፍ' ያሉን አስመልክተው ዛሬ አንድ መግለጫ አውጥተዋል።
"ሁሉም ባለሞያ እና የኢትዮጵያ ህዝብ እንደሚያውቀው ላለፉት 29 ቀናት ንቅናቄው በጥንቃቄ እንዲሁም ህጋዊና ጨዋነት በተሞላበት መንገድ ድህነታችንን እና ያለብንን ችግር የሚረዳ እና የሚመልስ መንግስት አለ ብሎ በማመን በቁጥር 12 የሚሆኑ የጤና ባለሞያውን አንገብጋቢ የህልውና ችግሮችን ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት በተዋረድ አስገብቶ መፍትሔ ሲጠባበቅ መቆየቱ ይታወቃል" ያለው መግለጫው ምንም ተስፋ ሰጭ ባልሆነና መሬት ላይ ተፈፃሚ ያልሆነ አንድ መግለጫ ይሉት ቃለ ምልልስ ብቻ በመስጠት የተሰጡት 30 ቀናት መገባጀጃ ላይ እንገኛለን ብሏል።
"በገባነው ቃል መሰረት የተሰጡት ቀናት ሲያበቃ አገልግሎት መስጠት እንደምናቆም ንቅናቄው ደጋግሞ አስጠንቅቋል። ጊዜውም ደረሰ እቅዳችንም ከነገ ማለትም ግንቦት 05/09/17 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ተፈፃሚ ይሆናል ብለን እናምናለን። መንግስት ለህዝብ ምንም ደንታ እንደሌለው በመረዳት ሆስፒታሎችን እና ሌሎች የጤና ተቋማትን ሙሉ በሙሉ በመዝጋት ሊደርስ የሚችለውን የህዝባችንን እልቂት ለመቀነስ ድንገተኛ ክፍሎች ክፍት እንዲሆኑ ንቅናቄው ወስኗል" የሚለው መግለጫ እነዚህን ከፊል አገልግሎት የምንሰጠው የጊዜ ገደብ ከመንግሥት በሚሰጠን ምላሽ ላይ የተመረኮዘ ይሆናል ብለዋል።
"በየትኛውም አካባቢ በባለሞያዎች ላይ እስር፣ አካላዊ ጉዳት ማድረስ እና ማሳደድ የሚኖር ከሆነ ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት ለማቋረጥ ልንገደድ እንደምንችል መንግሰት እና ውዱ ህዝባችን ሊገነዘብ ይገባል" በማለት አቋማቸውን ገልፀዋል።
የጤና ባለሙያዎቹ አጥጋቢ እና ተጨባጭ መልስ እስከሚሰጣቸው ድረስ በሚከተሉት የስራ ክፍሎች ብቻ አገልግሎት እንደሚሰጡ ይፋ አርገዋል:
የአዋቂ እና የህፃናት ድንገተኛ ክፍሎች
የአዋቂና የህፃናት ፅኑ ህሙማን ክፍሎች
የማዋለጃ ክፍሎች
"ይሁንና የፀጥታ አካላት የሀይል አማራጭ የሚጠቀሙ ከሆነ ሀገሪቱ ወዳልተፈለገ ግጭት እንዳትገባ እና ሌላ አላማ ያላቸው አካላት እንዳይገቡ ጥንቃቄ ይደረግ፣ ወደ ስራችን የሚመልሰን የጥያቄያችን ትክክለኛ ምላሽ እንጅ መሳሪያ ወይም የመንግስት ማስፈራሪያ አይደለም" በማለት አሳውቀዋል።
መረጃን ከመሠረት!
መሃይም የሞላት ሀገር መጨረሻዋ ምን ይሆን?