(መሠረት ሚድያ)- በሐቅ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ሥር የሚተዳደረው “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የበይነመረብ ሚዲያ መሥራች እና ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ ዛሬ አርብ ሰኔ 6 ቀን፤ 2017 ከእስር መፈታቱ ታውቋል።
በኢትዮጵያ ካሉ የካበተ ልምድ ካላቸው ጋዜጠኞች አንዱ የሆነው ተስፋለም ወልደየስ 'ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት' በሚል ተጠርጥሮ መታሰሩ ይታወሳል።
በአዲስ አበባ ከሚገኘው ግዮን ሆቴል ቅጥር ግቢ ውስጥ ሲቪል በለበሱ የፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር የዋለው ተስፋለም የመጀመርያውን ቀን ሌሊት እስጢፋኖስ አካባቢ በሚገኝ የፖሊስ መምሪያ ሕንፃ ውስጥ ወንበር ላይ እንዲያሳልፍ መደረጉን ሐቅ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ገልጿ ነበር።
የመጀመሪያውን ሌሊት ካሳለፈበት እስጢፋኖስ አካባቢ ከሚገኝ የፖሊስ መምሪያ በነጋታው ሰኔ 2 ቀን፤ 2017 ቄራ አካባቢ ወደሚገኝ የፖሊስ መምሪያ ተዘዋውሮ የነበረ ሲሆን ቀጥሎም በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፣ ቂርቆስ ምድብ ችሎት ቀርቦ በ15,000 ብር ዋስትና እንዲፈታ ተወስኖ ነበር።
ይህ የዋስትና መብት ላይ ይግባኝ በመባሉ እስካሁን እስር ላይ ቆይቶ ነበር።
ተስፋለም በእስር ላይ በቆየባቸው ያለፉት ቀናት ከእስር እንዲፈታ ከሀገር ውስጥ እስከ አለም አቀፍ ተቋማት ጥሪ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።
መረጃን ከመሠረት!