የታዳጊ ወጣቶችን ህይወት ቁማር አስይዞ የሚደረግ ስደት፡ ተናጋሪም፣ መፍትሄም ያጣው ችግራችን
ገብረ ህይወት ባይከዳኝ ዘብሔረ ቡልጋ ለመሠረት ሚድያ (መሠረት ሚድያ)- ይህ ጽሁፍ የተዘጋጀው በአንድ የሀገሩ አፍላ ወጣቶች ህይወታቸውን በአስከፊ አደጋ ዉስጥ አስገብትው ከሀገራቸው ለመሰደድ አስከፊውን መንገድ የሚያውቁትን እና ያደጉበትን የትውልድ አከባቢያቸውን ለቀው ለመሰደድ እናም እልፍ ብሎልኝ የኔንም የቤተሰቦቼንም ህይወት አሻሽላለው በሚል ቀቢፀ ተስፋ መነሻቸውን ከተለያዩ የሀገራችን አከባቢዎች ያደረጉ ታዳጊ ወጣቶች የስደት ጉዞን ተመልክቶ ልቦናው ያዘነ እና ትኩረት እንዲሁም መፍትሄ የሚያስፈልገው ስር የሰደደ ጉዳይነቱ ባሳሰበው ዜጋ ነው።
ይህ ጽሁፍ መነሻውን ያደረገው እና የሚያተኩረው ከኮምቦልቻ - አፋር - ጅቡቲ ብሎም ሳዑዲ አረቢያ ባለው አስከፊ የስደት መስመር ላይ በየዕለቱ የሚታይ አሳዛኝ የወጣቶች የስደት ጉዞ መስመር ላይ ነው። ለጽሁፉ መረጃ ምንጭነትም መመልከትን (observation) እና መረጃዎችን አከባቢው ላይ በቋሚነት ለረዥም ጊዜ ከኖሩ ሰዎች በመጠየቅ የተሰናዳ የዳሰሳ ጽሁፍ ሲሆን በሳይንሳዊ ጥናት ወይም በቁጥር የተደረሰበት ነው ለማለት አያስደፍርም።
የጽሁፉ ዋና አላማም ስለጉዳዩ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን እንዲያውቁት ለማድረግ እንዲሁም ትኩረት የተነፈገው ይህ የዕለት ከዕለት ተግባር ስለ ሰብአዊነት ብሎም ስለ ሀገራችን ወጣቶች ስቃይ የሚገዳቸው ዜጎች ስለዚህ ጉዳይ ድምፃቸውን እንዲያሰሙ እንዲሁም ለመፍትሄው እንዲወያዩ እና መሬት ላይ ፍሬ የሚያፈራ ስራ እንዲሰራ እንደ መነሻ ለማሳሰብ ያህል ነው።
መንደርደሪያ፡ አንድ ሰው ከኮምቦልቻ ተነስቶ ወደ ሰመራ - ሎጊያ በህዝብ ትራንስፖርት ለስራ ወይም ለሌላ ጉዳይ ቢንቀሳቀስ የሚመለከተው አንድ ለየት ያለ (peculiar) ክስተት አለ። ይህም ክስተት ከተለመዱት የኬላ ላይ ፍተሻዎችና የትራፊክ ፖሊሶች ቁጥጥር ወጣ ያለ ነው።
ከኮምቦልቻ ተነስተው ሲጓዙ ባቲ፣ ቡርቃ፣ ካሳጊታ፣ ወይም ሚሌ ላይ ሲደርሱ የፌዴራል ወይንም የክልል ፖሊሶች መኪናውን አስቁመው ይፈትሻሉ። የሚፈትሹበት ምክንያት ግን ኮንትሮባንድ ዕቃ ወይንም የጦር መሳሪያ ይገኛል በሚል አይደለም።
እድሚያቸው ከ15 ዓመት ብዙም ያልዘለለ፣ በእጃቸው ምንም ያልያዙ ፣ በስደት ሳዑዲ አረቢያ ለመሄድ ረጅሙን የስደት ጉዞ በመጓዝ ላይ ያሉ ታዳጊዎችን ወይንም በአካባቢው አጠራር "ኮብላይ” ፍለጋ እንጂ።
እርስዎ የተሳፈሩበት ሚኒባስ መኪና አራት ወይንም አምስት ጊዜ ከጉዞው ቆሞ ወጣቶች በፖሊስ ተመርጠው ወጥተው መስቀለኛ ጥያቄዎችን ሲጠየቁ ማየት ለመንገዱ አዲስ ለሆነ ሰው ግር ቢያሰኝም በዚህ መስመር በተደጋጋሚ ለሚመላለስ ተጓዥ የተለመደ ሂደት ነው። ከላይ በመንደርደሪያው ላይ ያነሳሁት ነጥብ በጥቂት ሰዎች ለአንድ ጊዜ ወይም ለተወሰነ ድግግሞሽ ብቻ የተደረገ ሳይሆን በየጊዜው እየተደረገ ያለ እና ብዙ ሰዎችን የሚያሳትፍ ትስስር ያለው፣ የታዳጊ ወጣቶች ስቃይ በዓይን የሚታይበት የዕለት ተዕለት ጉዳይ ነው። ስለጉዳዩና ስለተሳታፊዎቹ በተወሰነ መልኩ ለመዘርዘር ልሞክር፡፡
ማነው የሚጓዘው?
በዚህ አስጨናቂና አስከፊ ጉዞ ላይ የሚሳተፉት በአብዛኛው ከደሴ እና አካባቢው ከሚገኙ ገጠራማና ከፊል ከተማ ቀመስ ቦታዎች ላይ የሚገኙ ታዳጊዎች ናቸው። እነዚህ ታዳጊዎች ስለጉዳዩ ከሁለት ምንጮች መረጃ ያገኛሉ። አንደኛው በየአካባቢው ከሚገኙ ደላላዎች (አስኮብላዮች) ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ካሁን በፊት በዚሁ መንገድ ተጉዘው ህይወታቸው እንደተቀየረ ከሚያስቧቸው ሌሎች ሰዎች ነው።
እንደሚገመተው አስኮብላዮች በጉዞው ላይ ስለሚያጋጥማቸው ስቃይ ሳይሆን ሳዑዲ አረቢያ ወይንም ሌሎች የአረብ ሃገራት ሄደው ስለሚያገኙት "ገንዘብ” ይሰብኳቸዋል። መስበክም ብቻ ሳይሆን ስለጉዞውና ስለፍተሻው ሁኔታ አስረድተው ምንም የማያውቁ ታዳጊዎች ወደ በረሃው ጉዞ እንዲገቡ ያደርጋሉ።
በዚህ ጊዜም ክፍያ አይጠይቋቸውም። አንድ ታዳጊ ስለጉዞው ከተስማማ በኋላ ለኪሱ የሚሆን አነስተኛ ገንዘብ (እስከ 2,000 ብር)፣ የቀበሌ ወይንም ዲጂታል መታወቂያ ብቻ፣ እንዲሁም ቅያሬ ልብስ እንኳን ሳይዝ፣ ሊጓዝ ስለተነሳበት ሀገር ሁኔታ፣ ስለሚጓዘው የመንገድ ረቀት እና ስለሚያልፍባቸው ቦታዎች ምንም አይነት መረዳት ሳይኖረው ስለጉዞው መዘጋጀት ይጀምራል።
አስኮብላዩ አንዳንድ ፍተሻ ላይ ሊጠየቁ የሚችሉ መስቀለኛ ጥያቄዎችን ያስጠናዋል። ከዛም ጉዞ ይጀመራል። ጉዞው በርካታ ቀናትን የሚወስድ ሲሆን ከከተማ ከተማ ከፍተኛ የትራንስፖርት ወጪ እየተከፈለበት፣ በአሰቃቂ ሁኔታ በሚያስመርር በርሃ ይደረጋል።
ልክ ባህር ከተሻገሩ በኋላ ወይንም ድንበር ላይ ሲደርሱ ወደ ቤተሰብ ተደውሎ ገንዘብ እንዲከፍሉ ይገደዳሉ። እኔ ባደረግኩት ማጣራት ለአንድ ተጓዥ መጠኑ ከ100 ሺህ እስከ 300 ሺ ብር ድረስ ይከፈልበታል።
ምን ያህል ውጤታማ ይሆናሉ?
እንደሚታወቀውና በርካታ ጊዜም እንደተዘገበው ደንበር ተሻግረው በሚጓዙበት ወቅት በርካቶች በጀልባ መገልበጥ ምክንያት ባህር ውስጥ ሰምጠው ህይወታቸው ማለፉ የተለመደ ሆኗል። ከዚህም በተጨማሪ በሚያልፉባቸው ሃገራት ባሉ ጦርነቶች ምክንያት በጦርነት ቀጠና ውስጥ የሚያልፉ ሲሆን ሳዑዲ ድንበር በሚደርሱበት ጊዜም ቢሆን ከተያዙ ያለምንም ጥያቄ ወደ ሃገር ቤት እንዲመለሱ ይደረጋል።
በለስ ቀንቷቸው ሳዑዲ አረቢያ የገቡትም እንኳን ቢሆኑ ህጋዊ የመኖሪያ እና የስራ ፍቃድ ማግኘት እጅግ ከባድ ስለሚሆንባቸው ከቤት ዉጪ ያለ ፍቃድ ሲንቀሳቀሱ ወይም በጥቆማ ከተያዙ እንኳን የሰው ልጆች ይቅርና ለዕቃ ሳይበላሽ ለማስቀመጥ የማይቻልበት ማጎሪያ መጋዘን እስር ቤት ዉስጥ ከብዙ መሰሎቻቸው ጋር እንዲወረወሩ ይደረጋል።
በስንት ለቅሶ እና ልመና በኋላ ተራ በተራ ከችግሩ አንፃር በጣም ጥቂት በጥቂቱ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ይደረጋል። የሚያሳዝነው ግን በዚህ ሁኔታ ከሳዑዲ የተመለሱ ዜጎች በድጋሚ በዚሁ ሁኔታ ወደ ስደት ለመጓዝ ሲሞክሩ ማየት ነው።
ምክንያቱ ምንድነው?
ለዚህ አሰቃቂ የታዳጊዎች የበርሃ ስደት ጉዞ በርካታ ምክንያቶችን ማንሳት ቢቻልም እኔ ሁለቱ ውሃ የሚያነሱ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ።
አንደኛው ስር የሰደደ የኢኮኖሚ ችግር ሲሆን በርካታ ታዳጊዎች በአጭር ጊዜ ለመለወጥ በማቀድ ህይወታቸውን አደጋ ላይ የሚጥል ስደት ላይ ሲሳተፉ ይታያል። ሁለተኛና እኔ በጣም ትልቅ አስተዋጾ አለው ብየ የማስበው የታዳጊዎቹ የእውቀት ማነስና የሚያስተምር የተሻለ (role model) ማየት አለመቻል ነው ብየ አስባለሁ።ይህን ለማለት ያስደፈረኝ ጉዳይ በርካታ ከላይ የተጠቀሱት አከባቢ ታዳጊዎች ወደ ሳዑዲ ከመሄድ ውጪ ሌላ አማራጭ ያለ እስከማይመስላቸው ድረስ የተሻለ አርአያ ማጣታቸውን በመመልከት ነው።
ሌላኛውና በቅርቡ እየታየ ያለው የሰላም ማጣት የራሱ የሆነ ድርሻ ያለው መሆኑ አይዘነጋም። ምን ቢደረግ ወጣቶቹን ከዚህ አስከፊ ችግር እንዲድኑ ማድረግ ይቻላል? የእህት እና ወንድሞቻቸው አስከፊ ስቃይ የሚገዳቸው ዜጎች ድምፃቸውን በማሰማት እንዲሁም ሃሳብ በማዋጣት እኚህ ወጣቶች ከዚህ የችግር አዙሪት እንዲድኑ ግንዛቤ የሚያገኙበትን ሁኔታዎች በተቻለ ሁኔታ በመፍጠር እንዲሁም አሁንም ያሉትን ተፅዕኖ ፈጣሪዎችን (በየ አከባቢው ያሉ ወጣቶቹ አይተዋቸው እንዲጓጉ የሚደረጉ በስደት የሚኖሩትን ጨምሮ ያለፉበትን ሁኔታ በቀናነት እንዲያካፍሉ ዕድል በማመቻቸት) እና በማስተባበር ወጣቶቹ ግንዛቤ እንዲያገኙ ማድረግ ማድረግ የተገባ ይሆናል።
በወጣቶች እና ህፃናት ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ እና በዚህ ዙሪያ እነዲሁም ተያያዥ ስራዎችን የሚሰሩ ህብረቶች ተቋቁመው ካሉ በማጠናከር ከሌሉም በመፍጠር እና በማቋቋም፣አባል በመሆን፣ በመሳተፍ እና በተለያዩ መንገዶች በመደገፍ ትብብርን በማድረግ ሌሎች እኔ ባላወቅኳቸው እና ባልጠቀስኳቸው መስመሮች እና አከባቢዎች የሚደረጉ ትውልድን የጠመደ የስቃይ እና እንግልት ድርጊትን ለመከላከል እንዲሁም ለማስቀረት በትብብር የእኔም ጉዳይ ነው በማለት በቁጭት ለመስራት መነሳት እና ከህሊና ወቀሳም ሆነ ትውልድን ከአስከፊ እንግልት እና ችግር እንዲድን መረባረብ ይገባናል።
ገብረ ህይወት ባይከዳኝ ዘብሔረ ቡልጋ
Photo: File