በጉዱ ካሳ ለመሠረት ሚድያ
(መሠረት ሚድያ)- ግንቦት 30 በዓለም ዙሪያ ያሉ ኢትዮጵያውያን አንድ ብርቅዬ ነገር ለማየት ችለዋል፣ ብዙዎች ከቶም ሊሆን አይችልም ያሉት ሃሳብ ነው- አንድነት:: ይህ አንድነት የወለደው የጋራ ስቃይ እና የሰላም እጦት ነው።
አብሮነት ኢትዮጵያ ከርዕዮት ሚዲያ ጋር በመተባበር ታላቅ የተቃውሞ የኢንተርኔት ትእይንተ ህዝብ ግንቦት 30 አዘጋጅቶ ነበር:: ዝም ብሎ የሚታይ ትእይንተ ህዝብ ብቻ አልነበረም። የኢትዮጵያን ፖለቲካ ለብዙ አስርት አመታት ሲያምስ የቆየን ክፍፍልን እና ጥርጣሬን የሰባበረ ነው::
በሀገሪቷ የተለያዩ ስፍራዎች የሚካሄዱ ጦርነቶች በቀጠሉበት፣ ጋዜጠኞች ለእስር በተዳረጉበት፣ የሀገሪቷ የፖለቲካዊ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተባብሰው በቀጠሉበት በዚህ ሰአት የተካሄደው የኢንተርኔት ትእይንተ ህዝብ አንድ መልእክት የያዘ ነበር:: "ጦርነት ይቁም! አገዛዝ ያብቃ! ሰላም ይምጣ!" የሚል::
“እነዚህ ግለሰቦች በተለመደው ሁኔታ ተመሳሳይ መድረክ ሊጋሩ ስለመቻላቸው በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም”
ትእይንተ ህዝቡን ታሪካዊ የሚያድርገው መልእክቱ ብቻ አይደለም:: ከዚህ መልእክት ጀርባ ያሉ አንደበቶች ትእይንተ ህዝቡን ታሪካዊ አርገውታል:: ትእይንተ ህዝቡ የርእዮተ አለም ልዩነት አላቻው የሚባሉ የተለያዩ የፖለቲካ እሳቤዎችን እና የብሄር ቡድኖችን የሚወክሉ ሰዎች መድረክ እንዲጋሩ አርጏል:: ይህ ከአብዮታዊነት አንሶ ሊታይ አይችልም::
እነዚህ ግለሰቦች በተለመደው ሁኔታ ተመሳሳይ መድረክ ሊጋሩ ስለመቻላቸው በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም:: እንዲያውም አንዳንዶች በፖለቲካዊ ክህደት ወይንም በአመፅ ቀስቃሽነት እርስ በርስ የተወነጃጀሉ ናቸው:: ይሁንና አሁን አብረው ቆመዋል::
ለምን? ምክንያቱም ከርእዮተ አለም ልዩነት ክፍ ያለ አደጋ ፊታቸው ተደቅኗል- የሀገሪቷ ህልውና እና የዜጎች ቀጣይ ህይወት:: ይህ ለታይታ የተካሄደ አንድነት ሳይሆን አስፈላጊ የሆነ አንድነት ነው:: ይህ አይነቱ አንድነት ቀጣይነት ካለው: ከስልጣን ህዝብን ያስቀደመ ፖለቲካዊ ብስለት ጅማሬ ተደርጎ ሊታይ ይችላል::
መንግስት "ይቺ ባቄላ ካደረች አትቆረጠምም" በሚል ብሂል ዩትዩብን ለተወሰነ ሰአት ሲዘጋ እንደነበር የኢንተርኔት ትእይንተ ህዝቡ አዘጋጆች ሲናገሩ ነበር:: ጉዳዩ መንግስትን ምን ይህል እንዳስቆጣና ስጋት ላይ እንደጣለው አመላካች ነው::
በስልጣን ላይ ያሉትን ሰዎች ስጋት ውስጥ የጣላቸው ትእይንተ ህዝቡ ብቻ አይደለም:: የተለያዩ የፖለቲካ መሪዎች የብሄር ሰንሰለታቸውን በጥሰው በአንድ ተሰባስበው ስለ ሰላም አስፈላጊነት መናገራቸው ነው::
ምላሹ ሁላችንም ቀድሞም የምናቀውን ሃቅ ያረጋገጠ ነው- እውነት የመንግስት ትልቁ ስጋት መሆኑን: ሰዎች የህብረት እና የአንድነት ድምፅ ሲያሰሙ መራዳቸውን:: ትእይንተ ህዝቡ "ኢትዮጵያውያን ካሁን በሁዋላ በጭራሽ በጋራ አይቆሙም" የሚለው ሃሳብ ያፈራረሰ ነው:: በጋራ ቆመዋል:: በጋራ መቆም ይችላሉ:: በጋራ መቆምም አለባቸው::
ከሁሉ በላይ ግልፅ የሆነው : የሰላም ጥያቄ ከአንድ ወይንም ከሌላ ስፍራ የመነጨ ሳይሆን ከሁሉም ቦታ የመጣ መሆኑ ነው:: ከሁሉም ቦታ የሰላም ጥያቄ ሲመጣ መሀሉ ሊሰማ ይገባል አለዚያ መፈረካከሱ ነው::
ጥያቄው መንግስት ጥያቄውን ሰምቶ የማስተካከያ እርምጃ ይወስዳል ወይ የሚለው ነው:: በትእይንተ ህዝቡ ላይ የተሳተፋችሁ የፖለቲካ መሪዎች ተደራጁ፣ ፃፉ፣ ህዝብን አስተምሩ፣ ተቋውሟችሁን ማሰማት ቀጥሉ::
በዝምታ ያያችሁ ሰዎች ዝምታቹ ከመስማማት ይቆጠራል እና ድምፃችሁን አሰሙ:: በስልጣን ላይ ያላችሁ ሰዎች ሰላምን የመምረጥ ግዜያችሁን አታባክኑ።
መረጃን ከመሠረት!
** ለዚህ ምላሽ የሚሆንም ይሁን በሌላ ማንኛውም ጉዳይ ላይ አስተያየት ያለው ለሚድያችን በዚህ ኢሜይል መላክ ይችላል: info@meseretmedia.org