መሀል አዲስ አበባ ላይ አንድ የፖሊስ አባል ክላሽ በመጠቀም ህዝብ ፊት ግድያ መፈፀሙ ታወቀ
(መሠረት ሚድያ)- ባሳለፍነው ሀሙስ እለት በርካታ ድርጊቱን የተመለከቱ ሰዎችን ያስደነገጠ፣ ያሳዘነ እና ያስለቀሰ ግድያ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በተለምዶ 'አፍንጮ በር' ተብሎ በሚጠራው ስፍራ መፈፀሙ ታውቋል።
ጉዳዩ እንዲህ ነው፣
በእለቱ ከቀኑ 7:50 ገደማ አንድ የፖሊስ አባል አፍንጮ በር አካባቢ ሌላ ግለሰብን ሁለት ግዜ ጭንቅላቱ ላይ ክላሽንኮቭ በመተኮስ ገድሏል። ግድያው ሲፈፀም በርካታ ሰዎች የተመለከቱ ሲሆን ፖሊሱ ግድያውን ከፈፀመ በኋላ በመሮጥ ሸሽቷል።
በአካባቢው የነበሩ የአይን እማኞች ምን አሉ?
"ከአራዳ ጊዮርጊስ አቅጣጫ ወደ አራዳ ጊዮርጊስ እየነዳን ነበር። አፍንጮ በር ድልድዩ ጋር ከመድረሳችን በፊት አንድ ፖሊስ ሁለት ግዜ ተኩሶ ሰው ሲገድል ተመለከትን። ሟቹ የጎዳና ተዳዳሪ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አለን። የተኮሰው ከጀርባ ሆኖ ነው። በድንጋጤ እሳው ፈዘን ቀረን። ሟቹ ወዲያው በግንባሩ ወደቀ።
"አጭር ቪድዮ ወስደናል። ወዲያው ከመኪና መውጣት ሰጋን ምክንያቱም ገዳዩ ፖሊስ የተለየ ባህሪ ያሳይ ስለነበር ለራሳችንም ሰጋን። አንዴ ወደላይ፣ ከዛ ወደታች ይሮጣል። ከዛ ሰው መሰባሰብ ጀመረ፣ ለአንድ ትራፊክ የሆነው ነገርን። ከዛም መኪናውን ራቅ አርገን ወስደን ሁለታችን ሰው ወደሞተበት ቦታ ተመለስን። በወቅቱ የትራፊክ ፖሊሱ ገዳዩን ፖሊስ እያዋራው ነበር። በዛ ቅፅበት ፖሊሱ ለአንድ ሌላ ሴት ፖሊስ መሳርያውን ሰጥቶ ከስፍራው በሩጫ ሲያመልጥ አየን።"
"በርካቶች በሩጫ ተከተልነው። ሰባ ደረጃ አካባቢ በአንድ ታክሲ ተሳፍሮ አመለጠ። ሴት ፖሊሷ ገዳዩ የራስ ደስታ ፖሊስ ቅርንጫፍ ባልደረባ እንደሆነ ነገረችን። ከዛ በኋላ ነበር ተጨማሪ ሀይል በፓትሮል የመጣው። ከዛ በሀይል ከቦታው እንድንበተን አረጉ።"
"ቢያንስ ሬሳውን በጨርቅ ሸፍኑት ስንላቸው ቁጣ በተቀላቀለበት መልኩ አባራሩን። የሟቹ ደም ረግቶ የሚያሳዝን ነገር ህዝብ ሲያይ ነበር። ይህ ሁሉ ሲሆን አምቡላንስ አልመጣም ነበር። አንዳንዱ ምንም ያልመሰለው ነበር በስፍራው። በጣም አሳዛኝ ቀን ነበር።"
በዚህ ዙርያ ከአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ የጠየቅን ሲሆን ዝርዝር መረጃ ከደረሰን ይዘን እንመለሳለን።
መረጃን ከመሠረት!