ፓርላማው ያጸደቀው 'በሽፋን ስር ሆኖ ምርመራ ማድረግ' ከመግደል መለስ ሌሎች ወንጀሎችን የሚፈቅደው ድንጋጌ 'እንዲሁም ጤዛ ነሽ ሊያውም ዘንቦብሽ' ነው
በያሬድ ሀይለማርያም የተፃፈ
(መሠረት ሚድያ)- ከትናንት በስቲያ በሕገ ወጥ መልኩ የተገኘን ንብረት ለራስ የማድረግ እና የሽብር ወንጀልን በሽፋን ስር ሆኖ ምርመራ ስለማድረግ (undercover investigation) አስመልክቶ ፓርላማው ባጸደቀው አዋጅ አንቀጽ 26(4) ላይ አንድ አነጋጋሪ ድንጋጌ ተቀምጧል።
እሱም “በዚህ አዋጅ መሰረት በሽፋን ስር የሚደረግ ምርመራ ወይም በቁጥጥር ስር የሚደረግ ማስተላለፍን እንዲያስፈጽም የተመደበ ሰዉ በግዴታው ላይ እያለ ከአቅሙ በላይ በሆነ ምክንያትና ከፈቃዱውጭ ሆኖ ከግድያ ወንጀል በስተቀር ለሚፈጽመው የወንጀል ድርጊት የወንጀል ክስ አይቀርብበትም” የሚል ነው።
ይሄ አንቀጽ ትልቅ ክፍተት እና ለዘፈቀደ ትርጓሜ በር የሚከፍቱ ሃሳቦችን የያዘ ከመሆኑም በላይ ወንጀል መርማሪዎች ያሻቸውን እንዲያደርጉና የዜጎችን መብት ያለገደብ የሚጥሱ ተግባራትን ያለ ምንም ተጠያቂነት እንዲፈጽሙ የሚያደርግ ነው።
እጅግ መረን በለቀቀና በተበላሸ አሠራር ላይ እንዲህ ያለ የዜጎችን መብት አደጋ ላይ የሚጥል ፈቃጅ ሕግ ማውጣት ሊያውም ዘምቦብሽ ነው የሚያስብለው።
በሽፋን ስር ሆኖ ምርመራ ስለማድረግ (undercover investigation) በመላው አለም የሚተገበር የወንጀል ምርመራ ሂደት ስልት ነው።
ነገር ግን በሌሎች አገሮች፤ የአሜሪካውን FBI ጨምሮ ለዚህ አይነቱ ምርመራ በጣም ጥንቃቄ የተሞላበት እና ጥብቅ የሆነ የሥነ ምግባርና የተጠያቂነት መመሪያ (guidelines) ተዘጋጅተው የሚከናወኑ ናቸው።
መመሪያዎቹ ከሚይዟቸው ነገሮች አንዱ መርማሪዎች በተቻላቸው መጠን ወንጀል ወይም ሕገ ወጥ ተግባራትን እንዳይፈጽሙ ወይም መጠነኛ ከሆነ ሕገ ወጥ እርምጃ እንዳያልፉ መከላከል ነው፣ minimizing illegal activities ለመርማሪዎቹ የሚቀመጥ አንዱ ገደብ ነው።
ሌላው የሽፋን ሥራዎቻቸው ethical consideration እና safety ዋነኛ መርሆቻቸው ናቸው። በየሜዳው የጠረጠረውን ሁሉ ይዞ የሚነርት መርማሪ ባለበት አገር ይህ አንቀጽ ለወንጀለኛ መርማሪዎች የሥራ ፈቃድ ሠርተፊኬት እንደመስጠት ነው።
ሰሞኑን መነጋገሪያ የነበረው የገለቴ ባል ታስሮ የነበረበትን መንገድን ማየት በቂ ነው። እሷ በሰይፉ ሾው ቀርባ ባቀረበችው ሮሮ የተነሳ በማግስቱ ሲቪል የለበሱ የደህንነት አባላት ግለሰቡን ይዘው አይኑን በጨርቅ ጨፍነው፣ ከመኪና መኪና እያገላበጡ ወዳልታወቀ ሥፍራ ወስደው፣ ክፉኛ ደብድበው፣ የአካል ጉዳት አድርሰው፣ ከወገቡ በላይ እርቃኑን ፎቶ አንስተው፣ ያነሱትን ፎቶ በማህበራዊ ድህረ ገጽ አሰራጭተው፣ ንብረቱን ነጥቀው፣ ከቀናት ቆይታ በኋላ ለቀውታል።
እንግዲህ ለእነዚህ አፋኝና ሕገ ወጥ መርማሪዎች ነው ከመግደል መለስ ያሻችሁን ወንጀል ፈጽሙ የሚል የሕግ ሽፋን የሚሰጠው።
ከላይ የጠቀስኩትና አሁን የጸደቀው አዋጅ ግን በተቃራኒው maximizing criminal and illegal activities ወይም የወንጀል ሥራዎችን የሚያደፋፍረና ከተጠያቂነትም የሚያስመልጥ ነው። ሕጉ፤
1ኛ/ ከአቅሙ በላይ በሆነ ምክንያትና ከፈቃዱ ውጭ ሆኖ የሚለው ሃሳብ በግልጽ ያልተቀመጠ በመሆኑ ለትርጉም የተጋለጠ ነው። የቶቹ ሁኔታዎች ናቸው ከመርማሪው አቅም ወይም ፈቃድ ውጪ ተብለው የሚበየኑት የሚለው ግልጽ አይደለም።
2ኛ/ 'ከግድያ ወንጀል በስተቀር ለሚፈጽመው የወንጀል ድርጊት የወንጀል ክስ አይቀርብበትም' የሚለው እጅግ አደገኛ አገላለጽ ደግጋሞ መርማሪው ከግድያ መልስ በተመርማሪው ላይ የማሰቃየት ወይም torture፣ ጾታዊ ጥቃት፣ ሙስና፣ ዝርፊያ፣ አፍኖ መሠወር፣ ወዘተ ... የመሳሰሉ አሰቃቂ ወኔጀሎችን ቢፈጽም አይጠየቅም ማለት ነው።
ይሄ ደግሞ 'እንዲሁም ጤዛ ነሽ ሊያውም ዘንቦብሽ' አይነት ነገር ነው የሚሆነው።
*መሠረት ሚድያ ላይ የሚቀርቡ አስተያየቶች በሙሉ የፀሀፊዎቹ እንጂ የሚድያው አቋም እንዳልሆኑ ልናስታውስ እንወዳለን።
መረጃን ከመሠረት!
Back to...