የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ከሀላፊነታቸው ለቀቁ
(መሠረት ሚድያ)- የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግስቴ ከሃላፊነታቸው መልቀቃቸው ተሰምቷል።
አቶ ጌታቸው በባለስልጣኑ በሃላፊነት ባገለገሉባቸው ባለፉት ሶስት አመት ተኩል የሃገሪቱን የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ሪፎርም ፕሮግራም በመንደፍ ሰፊ የፖሊሲ እና የመመርያ ስራዎችን እንዳከናወኑ ባልደረቦቻቸው ይመሰክሩላቸዋል በማለት ኢትዮ የንግድ እና ኢንቨስትመንት መድረክ ዘግቧል።
ቀደም ሲል አቶ ጌታቸው የትራንፖርት ሚኒስትር ዴኤታ በመቀጠልም በሞንትሪያል ካናዳ በሚገኘው የአለም አቀፍ የሲቪል አቪየሽን ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ ተወካይ ሆነው አገልግለው ነበር።
አቶ ጌታቸው በዳካር፣ ሴኔጋል የሚገኘው የአፍሪካ ሲቪል አቪዬሽን ኮሚሽን ለስራ ተወዳድረው የአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ዳይሬክተር ተደርገው መቀጠራቸው ታውቋል።
በአቶ ጌታቸው ምትክ የሲቪል አቪዬሽን የአየር ትራፊክ ማኔጅመንት ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ዮሃንስ አበራ በምትካቸው እንደተሾሙ ታውቋል።
ምናልባትም በሲቪል አቪዬሽን የመጨረሻ ስራቸው በሆነው በዛሬው እለት አቶ ጌታቸው የአቪዬሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ በኢትዮጵያ ለመገንባት የሚያስችል ስምምነት ፈርመው ነበር።
ዛሬ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣንና አይ ቲ ፓርክ (IT Park) ኢትዮጵያ የአቪዬሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ ለመገንባት የመግባቢያ ሰነድ የተፈራረሙ ሲሆን አቶ ጌታቸው መንግስቴ "በአይ ቲ ፓርክ ውስጥ የአቪዬሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ ለመገንባት የሚደረገው የጋራ ስምምነት የሃገሪቱ የአቪዬሽን ኢንዲስትሪ መጻኢ ዕድል ላይ ትልቅ ሚና አለው" ብለው መናገራቸውን ሚድያዎች ዘግበው ነበር።
Via ኢትዮ የንግድ እና ኢንቨስትመንት መድረክ
መረጃን ከመሠረት!