(መሠረት ሚድያ)- በአንዳንድ የአዲስ አበባ እስር ቤቶች የሚፈፀመው ወንጀሎችን እና በደሎችን ለማመን ያስቸግራል። ሚድያችን ዜጎች በተለያየ ክስ ተይዘው እስር ቤት ከገቡ በኋላ ምን እንደሚያጋጥማቸው ዳሰሳ አርጓል፣ እንዲህ እንቃኘዋለን።
ለደህንነቱ ሲባል ስሙን የማንጠቅሰው የመጀመርያው የመረጃ ምንጫችን መርካቶ እቃ በመሸከምና አልፎ አልፎም በመላላክ አራት ቤተሰብ እንደሚያስተዳድር ይገልፅና ታሪኩን እንዲህ ያስረዳል።
"እኔ ፍጹም ድሀ ነኝ። መጋቢት ወር መጨረሻ ላይ መገናኛ አካባቢ አንድ ሲቪል የለበሰ እና ሰውነቱ በስፖርት የዳበረ ወጣት ባስ ከምጠብቅበት ምሽት 1:00 ላይ ጠራኝ። አቤት አልኩት፣ መታወቂያ አለኝ። የአዲስ አበባ መታወቂያ ሰጠሁት፣ ስልኬን ተቀበለኝ። ሰጠሁት ስልክ ዳታ የለውም ካርድ ሙላ አለኝ፣ የ50 ብር ካርድ ሞላሁ።
በስልኬ ውስጥ ያለውን ነገር ካየ በኋላ ምንም ነገር ማግኘት አልቻለም። ሆኖም እኔን በአይኑ እየገላመጠ ፎቶ ጋለሪ ውስጥ ልሙጥ ባንድራ ዳውሎድ አድርጎ ልሙጥ ባንዲራ ይዘሀል እና በቁጥጥር ስር ውለሀል አለኝ። ለመናገር ስሞክር በጥፊ መታኝ፣ ደነገጥኩ። ኧረ እኔ ስለፖለቲካ የማውቀው ነገር የለኝም፣ ልጆች አሳዳጊነኝ ብዬ እንባዬን እያነባሁ ስለምነው 'አይ ሾላ ማረሚያ ትገባለህ፣ ካልሆነ 3,000 ብር ክፈል' አለኝ።
እኔ ምንም የለኝም ስለው በቀጥታ ሾላ ወስዶ ማረሚያ አስገባኝ፣ በጣም ድንጋጤ ፍርሀት ይታይብኛል። ማረሚያ ውስጥ ስገባ በርካታ ወቅታዊ ታፋሾች፣ የማውቃቸው ነጋዴዎች፣ ባለሙያዎች፣ አመራሮች፣ ወዛደሮች፣ ሌቦች እና የሌባ ተቀባዮች (በነሱ አጠራር የእጅ ባለሙያ) ብቻ የሌለ የለም። ታሳሪዎቹ በአብዛኛው የአማራ እና ትንሽ የወላይታ ተወላጆች ናቸው። አሁን ፍርሀቴ ለቀቀኝ፣ ከእኔም የባሱ ታሳሪዎች አሉ ብዬ ተፅናናሁ።"
የሌላኛው ታሳሪ ታሪክ:
የምዕራብ ጎጃም ዳንግላ ወረዳ አዲስ ኪዳን ተወላጅ ነው። አጋጣሚ ሊያገባ ወደ አገሩ ሊሄድ የባስ ትኬት ቆርጦ፣ አልጋ ይዞ ካለበት እቃ ገዛዝቶ ሲገባ ቀበቶህ የፋኖን ይመስላል ተብሎ እንደተያዘና ከፍተኛ ገንዘብ ተጠይቆ መክፈል እንዳልቻለ ተናግሯል። ስለ ሰርጉ ሲያወራ ሌሎች ታሳሪዎች እያለቀሱ እንደሰሙት ይናገራል።
ሶስተኛው ባለታሪክ ደግሞ የካ ክ/ከተማ ውስጥ የሚሰራ የመንግስት ሰራተኛ ነው።
የተያዘው ከቢሮ እንደሆነና የአንዳንድ ሚድያዎችን ፖስት ላይክ አድርገሀል ተብሎ እንደሆነ ያስረዳል። እሱ ግን ላይክ እንዳላረገ እና አንድ የተጣላው ሰው ተመሳሳይ አካውንት ከፍቶ ላይክ አድርጎ እና ስክሪንሹት በማድረግ እንዳስያዘው ያስረዳል።
አራተኛ ታሳሪ ደግሞ ይህን ይመስላል: የየካ ክ/ከተማ የሚሰራ የብልፅግና አመራር ነው። የታሰረበት ምክንያት ደግሞ በስራ ምክንያት የተጣላት አንድ አመራር እሱ መድረክ የሚመራበትን ስብሰባ ከጀርባው በፎቶሾፕ 'ድል ለጀግናው ፋኖ' ብላ እንዳቀናበረችበትና ስክሪንሹት አድርጋ እንዳሳሰረችው ይናገራል።
አምስተኛ ታሳሪ: ግለሰቡ የዛሬ አራት አመት መንግስት የክተት አዋጅ ሲያውጅ የዘመተ እና ብሬን የማረከ፤ የአማራ ክልላዊ መንግስት ሰርቲፊኬትና 60 ሺህ ብር የሸለመው መሆኑን ተናግሮ አሁን ላይ በንግድ ስራ ተሰማርቶ እንደሚተዳደር ያስረዳል። "ነገር ግን ሲቪል ለባሾች ገንዘብ ጠየቁኝ፣ አልከፍልም ብዬ ታሰርኩ" ብሏል።
መሠረት ሚድያ ባደረገው ማጣራት ሁሉም የሚታፈስ ሰው አማራጭ ይቀርብለታል: ወይ ገንዘብ ይከፍላል ካልሆነ ይታሰራል። "ዋናው ጉዳይ አንዳንዱ በዘመድና በእጅ መንሻ በ2 ቀን ይፈታል። የኔ ቢጤ ዘመድም፣ ገንዘብም የሌለው 20 ቀን ታስረን እንፈታለን። በቆይታዬ ማረሚያ ቤት ውስጥ የምትበላው የለም እንጅ ምንም አይነት ጥቃት አልደረሰብንም" የሚለው የመጀመርያው ባለታሪካችን እንደውም አንዳንድ ፖሊሶች እስከ መቼ ይሆን እያሉ ይበሳጫሉ ይላል።
"ማክሰኞ እለት በካቴና ታስረን በሽፍን መኪና ወደ ሌላ ቦታ ይወስዱናል። ለምን ስንል አቃቤ ህጎች ይመጣሉ እነሱ እንዳያዩ ይባላል። ፍርደኛ ታሳሪዎች ይሄን ሚስጥር ይነግሩልናል፣ ግን መፈታት የሚባል የለም" በማለት የደረሰበትን ያስረዳል።
ሁለተኛው ባለታሪካችን በዚህ ይስማማማል። "ስትታፈስ ቢዝነስ ይሰራብሀል፣ ወይ ለሲቪሎቹ ከፍለህ ትለቀቃለህ ወይ ለኢንስፔክተርና ኮማንደሮች ከፍለህ በ2 ቀንህ ትፈታለህ። ሌላውና ታላቁ ቢዝነስ ስትያዝ የተቀበሉትን ስልክ ካልከፈልክ በታሪክ አይመለስም፣ ብቻ ምን ልበልህ አንዱ ተበድሮ፣ አንዱ ከዘመድ አስልኮ ሌላው ጥሮ ግሮ የገዛው ስልክ አይመለስም" በማለት ሁኔታውን አስረድቷል።
አንዳንድ የመንግስት ሰራተኞቹ ከደሞዛቸው እየተቆረጠ በቴሌ ብድር የገዙት ስልክ እንደማይመለስላቸው ጭምር የጠቆሙት እነዚህ የቀድሞ ታሳሪዎች "እውነት መንግስት ይሄ መረጃ ያውቃል ወይ?" የሚል ጥያቄ አቅርበዋል።
አንደኛው ባለታሪክ በድጋሚ ይናገራል።
"እውነት ለመናገር ፍትህ ከስታለች እንጅ አለች፣ ፍ/ቤት ከቀረብክ ይለቁሀል፣ መርማሪዎች ይናደዳሉ። ግን ምን ያደርጋል ማን ወደ ፍትህ አደባባይ ያደርስሀል። እኔንም ስልኬን ቀምቶ ገንዘብ የጠየቀኝ የመርማሪ ሀላፊ ኢንስፔክተርና ኮማንደር አለ። ነገር ግን እኔ 8 ቀን ተመላለስኩ አሁን እንደሌሎቹ ተስፋ ቆረጥኩ። እቁብ ጥዬ የገዛሁትን ስልክ አይኔ እያየ አስረከብኩ። ለሀገሬ አንድ ነገር እንዳበረከትኩ እቆጥረዋለሁ። ስልኬ ይቅርብኝ፣ የኔ ጥያቄ ሲቪሎች በዚህ ልክ ገንዘብ እያሉ ከጠየቁ እስከሚጣራ የተያዘ ንብረት ካልተመለሰ መንግስትና ህዝብን እያራራቁት አይደለም ወይ? እውነት የላይኛው የመንግስት አካል ይሄን መሬት ላይ ያለ ግፍ ያውቀዋል ወይ?" ብሎ አስተያየቱን አጠቃሏል።
እኛም በዚህ ዙርያ ያሰባሰብነውን መረጃ በዚህ ቋጭተናል።
መረጃን ከመሠረት!
ቀላል ያውቀዋል እንዴ?