የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አውስትራሊያ በረራ ሊጀምር መሆኑ ታወቀ
(መሠረት ሚድያ)- የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሰማንያ አመት ታሪኩ አለምን ሲያዳርስ እስካሁን በረራ ወዳልጀመረበት ብቸኛው የአውስትራሊያ አህጉር በረራ ሊጀምር መሆኑ ተሰምቷል።
አየር መንገዱ ወደ አውስትራሊያዋ ሜልበርን ከተማ መደበኛ የመንገደኛ በረራ ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑን ኢትዮ የንግድ እና ኢንቨስትመንት መድረክ ዘግቧል።
በቅርቡ የሚከፈተው ይህ አዲስ የበረራ መስመር አፍሪካን ከአውስትራሊያ ጋር በማገናኘት ለንግድ፣ ቱሪዝም እና ኢንቨስትመንት ፍሰት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተገልጿል።
የበረራ መስመሩ ረዘም ያለ በመሆኑ አየር መንገዱ እንደ ኤርባስ A350 ወይም B787 ድሪምላይነር አውሮፕላኖችን እንደሚጠቀም ተጠቁሟል።
የአየር መንገዱ የስራ ሃላፊዎች ከሜልበርን ኤርፖርት አመራሮች ጋር በመነጋገር የቅድመ ዝግጅት ስራ በማከናወን ላይ መሆናቸው ታውቋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አውስትራሊያ በረራ ለመጀመር እቅድ የነበረው ከስድስት አመት በፊት ጀምሮ መሆኑን የመሠረት ሚድያ ምንጮች ጠቁመው ጉዞው ረዥም ሰዐት የሚፈጅ መሆኑ ትክክለኛውን የአውሮፕላን አይነት ማዘጋጀት አንድ ተግዳሮት እንደነበር ተጠቁሟል።
ይህ በረራ ከጀመረ በኋላ ምናልባት እንደ ሲንጋፖር ያሉ ከተሞች ላይ ትራንዚት አድርጎ እና ነዳጅ ቀድቶ ጉዞውን ሊያከናውን እንደሚችል ከወዲሁ ተገምቷል።
አየር መንገዱ አሁን ላይ ጠቅላላ አመታዊ ገቢው ከ7 ቢልዮን ዶላር የተሻገረ ሲሆን የአፍሪካ ትልቁ የመንገደኞች እና የጭነት (ካርጎ) እቃ አጓጓዥ ተቋም ሆኗል።
አሁን ላይ ከ150 በላይ የሆኑ መዳረሻዎች ያሉት አየር መንገዱ በአስደናቂ ፍጥነቱ አዲስ አበባ አፍሪካን ከሌላው አለም የምታገናኝ ከተማ አድርጓታል።
መረጃን ከመሠረት!