ኢትዮጵያ በኑሮ ውድነት ከአፍሪካ ቀዳሚዋ ሀገር መሆኗን አንድ ሪፖርት ጠቆመ
(መሠረት ሚድያ)- የኑሮ ውድነትን በአለም ዙርያ የሚከታተል አንድ ሪፖርት ኢትዮጵያ በኑሮ ውድነት ከአፍሪካ አንደኛ፣ ከአለም ደግሞ 53ኛ ሀገር እንደሆነች ጠቆመ።
ህዝቡ ከሚያገኘው ገንዘብ ውስጥ አብዛኛውን መሠረታዊ ለሚባሉ እንደ ምግብ እና ትራንስፖርት በማዋል ኢትዮጵያውያን ቀዳሚ እንደሆኑ የሚጠቁመው ይህ 'Cost of Living Index by Country 2025' የተባለ ሪፖርት ነው።
ሪፖርቱን ጠቅሶ APA የተባለው ሚድያ ዛሬ እንደዘገበው የዚህ ሪፖርት ውጤት የሚያሳየው ህዝቡ፣ በተለይ ቋሚ ገቢ ያላቸው ዜጎች መሠረታዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት እየተቸገሩ መሆናቸውን ነው።
በሪፖርቱ ከአፍሪካ ቦትስዋና፣ ሞዛምቢክ፣ አይቮሪ ኮስት እና ሶማልያ ቀጣይ እስከ 5 ያለውን ደረጃ ይዘዋል።
የቤት ኪራይ በኢትዮጵያ አሁን ላይ በንፅፅር ውድ የሚባል እንዳልሆነ ጠቅሶ ከኑሮ ውድነቱ ጋር ተያይዞ ሲሰላ ግን ለኢትዮጵያውያን ከፍተኛ መሆኑን ይጠቁማል።
"በሬስቶራንቶች መመገብ፣ ትራንስፖርት መጠቀም እና ሌሎች አገልግሎቶችን ማግኘት በከፍተኛ ደረጃ እየተወደደ መጥቷል። ለምሳሌ የሀገር ውስጥ ጉዞ ለማድረግ የሚጠይቀው ወጪ በብዙ የአፍሪካ ካለው ከፍ ያለ ነው" በማለት ሪፖርቱ ያብራራል።
ቪርጂን አይላንድስ፣ ስዊዘርላንድ፣ አይስላንድ፣ ባሀማስ፣ ሲንጋፖር፣ ሆንግ ኮንግ፣ ባርባዶስ፣ ኖርዌይ፣ ፓፓዋ ኒው ጊኒ እና ዴንማርክ በኑሮ ውድነት ከአንድ እስከ አስር ያለውን ቦታ ይዘዋል።
በዛሬው እለት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በነበረው አንድ ስብሰባ ላይ በሀገሪቱ የሚስተዋለውን የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት ተጨማሪ ስራዎች እንደሚያስፈልጉ ተነስቶ ነበር።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወ/ሮ አይሻ ያህያ የፍጆታ ዕቃዎች አቅርቦትና ስርጭትን በማረጋገጥና ህገወጥ የዋጋ ንረትን በመቆጣጠር ማህበረሰቡ ላይ የሚደርስ የኑሮ ውድነት ጫናን በመቀነስ የንግድ ስርአቱን የተሳለጠ ለማድረግ ተጨማሪ ስራዎች እንደሚያስፈልጉ ተናግረው ነበር።
መንግስት በቅርቡ ያደረገው የኢኮኖሚ ሪፎርምን ተከትሎ የብር የመግዛት አቅም መዳከሙ እና ይህ ያስከተለው የኑሮ ውድነት ከፍተኛ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
መረጃን ከመሠረት!