ኮሚሽኑ 'ውሸት ነው' ብሎ ያጣጣለው የመሠረት ሚድያ የመንግስት ሰራተኛ ቅነሳ ዘገባ እውነት መሆኑን ዛሬ አረጋገጠ
(መሠረት ሚድያ)- ሚድያችን ሰኔ 7/2017 ዓ/ም በሰራው አንድ ዘገባው ከጥቂት ወራት በፊት ከፀደቀው የመንግስት ሰራተኞች አዋጅ ጋር ተያይዞ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የመንግስት ሰራተኞች ከሀምሌ 1/2017 ዓ/ም ጀምሮ ከስራቸው ሊሰናበቱ እንደሆነ መዘገቡ ይታወሳል።
ይህን ተከትሎ በወቅቱ ለመንግስት ሚድያዎች አስተያየት የሰጡት የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር መኩሪያ ኃይሌ 'በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች' ሠራተኞች ይቀነሳሉ በሚል የሚናፈሰው መረጃ ትክክል እንዳልሆነ ተናግረው ነበር።
"ይህ ሪፎርም ከሰራተኛ ቅነሳ ጋር የተያያዘ ምንም ነገር የለውም። አዋጁን መስመር በመስመር ልታነቡት ትችላላችሁ የዚህ ሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ትልቁ ቁም ነገር የመንግስት ሰራተኞች መስራት ይችላሉ የሚል ፍልስፍና አለው" በማለት ኮሚሽነሩ ለመንግስት ሚድያዎች ተናግረው ነበር።
አክለውም "ሰራተኞች አመራር በማጣት ካልሆነ በቀር ችግሩ የመንግስት ሰራተኛ ነው የሚል ነገር አዋጁ የለውም። ስለዚህ ሪፎርሙ የሚያጠነጥነው ጠንካራ አመራር መፍጠር ነው፣ ለሰራተኛው ደግሞ ክፍተቱን መዝኖ ስልጠና መስጠት ነው" በማለት ተናግረዋል።
ይህን ተከትሎ በርካታ የመንግስት ሚድያዎች እና አክቲቪስቶች የመሠረት ሚድያን መረጃ ሀሰትነት ለማረገገጥ ብዙ ሲጥሩ ተመልክተናል።
ይሁንና የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነሩ ዶ/ር መኩሪያ ሀይሌ ከዚህ ቀደም የሰጡትን የ 'ሰራተኛ አይቀነስም' መግለጫ በሚጣረስ መልኩ ለመንግስት ሚድያዎች አሁን በሰጡት መግለጫ መንግስት ከሐምሌ 1 ጀምሮ የሽግግር ምዕራፍ አጠናቆ ወደ ትግበራ ምዕራፍ እንደሚሻገር ገልፀዋል።
ተቋሙ በአፍሪካ ልህቀት አካዳሚ ከሰኔ 27-29 ቀን 2017 ዓ.ም ለሠራተኞቹ ባደገረው የሽግግር ስልጠና ላይ ዶ/ር መኩሪያ እንዳሉት "ገንዘብ የምታሳድድ ከሆነ ሁል ጊዜ ችግር ውስጥ ነህ" ብለዋል።
“ተቋሙ በሪፎርሙ የመጀመሪያው ዌቭ የሽግግር ምዕራፍ ከገቡት ስምንት ተቋማት መካከል አራቱ ተቋማት የሽግግር ምዕራፉን በቀረበው የምዘና መስፈርት ስላሟሉ ወደ ተግባር ምእራፍ የተሸጋገሩ በመሆኑ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንም ከአራቱ አንዱ ሆኖ [ከሀምሌ 1 ጀምሮ] ወደ ተግባር ምዕራፍ ተሸጋግሯል እንኳን ደስ ያላችሁ" ብለዋል።
አክለውም ከሀምሌ 1 ጀምሮ "ከዝግጅት ምዕራፍ ወደ ተግባር ምዕራፍ ስለገባን ከወትሮ የተለየ ርብርብ ያስፈልገናል፣ ይህ ተቋም ሁለት ሥራ ነው የሚሰራው። አንዱ ራሱን መለወጥ ሁለተኛው ሌላውን መለወጥ አርአያ መሆን" በማለት አረጋግጠዋል።
“ሪፎርሙ የግድ መሳካት ስላለበት የሚወሰድ እርምጃ ይኖራል፣ የአገር ጉዳይ ከምንም ነገር በላይ ይበልጣልና ሰራተኛው እራሱን መጠበቅ መታመን መስራት ይጠበቅበታል። ከፊት ለፊቱ ይህ እንደሚኖር ማወቅ አለበት" በማለት ከስራ የሚቀነሱ ሰራተኞች እንደሚኖሩ ተናግረዋል።
ለሦስት ተከታተይ ቀናት የተሰጠውን ስልጠና የተካፈሉ የተቃሙ ሰራተኞች ሲቪል ሰርቪስ ከተመሰረተ ጀምሮ አይቶ የማያውቀው የሰራተኛ ቅነሳ እንደሚኖር እንደተነገራቸው ለሚድያችን ጠቁመዋል።
"እኛ ከመጀመርያቹ ስምንት ሰራተኛ ቀናሽ መስሪያ ቤቶች አንዱ ሆነናል። በሁለተኛ፣ ሶስተኛ፣ አራተኛ ወዘተ እየተባለ ሁሉንም ሰራተኛ እንደሚያዳርስ መረጃ አለን" በማለት የመሠረት ሚድያን ዘገባ ትክክለኛነት አረጋግጠዋል።
መረጃን ከመሠረት!