ጸሐፊው በአዲስ አበባ በሚገኙ የመንግስትና የግል ሆስፒታሎች የሚሰራ ሃኪም ነው
(መሠረት ሚድያ)- ቀደም ሲል መሠረት ሚድያ ላይ “የድንቁርና ጌቶች” በሚል ርእስ በሁለት ሀኪሞች በቀረበ ጽሁፍ አንዳንድ ፓስተሮች በጌታ ነገረኝ ስም የተሳሳቱና ማስረጃ የሌላቸው ድስኩሮችን እንደሚያሰራጩና ያልነቁ ሚስኪኖችን እንዴት እንደሚያጭበረብሩና እንደሚበዘብዙ አንብበናል፡፡
በአንባቢዎች ከተሰጡት አስተያያቶች አንዱ ማጭበርበሩና ብዝበዛዉ በፓስተሮች ብቻ ነው ወይ? በሌላ መስክ የለም ወይ? በጤናው መስክና ህክምና ላይ ማጭበርበር የለም ወይ? የሚሉ ይገኙበታል፡፡
እኔ በሙያዬ ሀኪም ነኝ። በጤናው መስክና ህክምና ላይ ማጭበርብር የለም ወይ? ለሚለዉ ጥያቄ ሙያው ዉስጥ እንዳለ ሀኪም የኔ መልስና እይታ ልክ ነዉ ማጭበርበሩና ብዝበዛዉ በሁሉም ዘርፍ ይመስላል፡፡ በዚህ ጽሁፍም በጤናው ዘርፍ በጣም ጥቂት በሆኑ ሃኪሞች የሚካሄዱ ጥቂት ግን አስነዋሪ የማጭበርበርና የብዝበዛ ተግባራትን ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡
በሃኪሞች ላይ ብቻ ያተኮርኩት በሁለት ምክንያቶች ነው፡፡
አንደኛው ጉዳዩ የተነሳዉ ፓስተር ዮናታን ያለምንም ማስረጃ የኢትዮጵያ ግማሹ ሀኪሞች ፎርጅድ ናቸው በማለቱ ስለሆነ እና ሁለተኛ “የድንቁርና ጌቶች” በሚል ርእስ የቀረበውም ጽሁፍም ለዛ መልስ ስለሆነ፤ ሁለተኛ እኔ በተሻለ መልኩ የማውቀውና ማስረጃ ያለኝ በጤና ዘርፉ ስላለው ችግር ስለሆነ ነው።
ምንም እንኳን አብዛኞቹ የጤና ባለሙያዎች የሙያ ስነ-ምግባራቸውን የሚጠብቁ ቢሆንም ከሙያው ውጪ በሆኑ ተግባራት እና ብዝበዛዎች የሚሳተፉ ጥቂት የጤና ባለሙያዎችም አሉ።
ለሰዉም ሆነ ለሙያው ደንታ የሌላቸዉ፤ ሆስፒታሎችን እንደ ሸቀጥ ሱቅ የሚጠቀሙ ጥቂት ግን በጣም ታዋቂ ሀኪሞች በደንብ አሉ፡፡ አንዳንዶቹ ከፍተኛ ወንጀል በሆኑ የህገወጥ የሰዎች ዝውውርና የአካል ሽያጭ ሰንሰለትም ውስጥም ይሳተፋሉ፡፡
እነዚህ አይነቶቹ የነቀዙ ሀኪሞች ማፊያ ሀኪሞች (የብዝበዛ ጌቶች) ይባላሉ፡፡
ማፊያ ዶክተሮቹ በአብዛኛው በትላልቅ ሆስፒታሎች የሚሰሩና በሙያ ደራጃቸውም በብዛት ስፔሻላይዝድ እና ከዛ በላይ ያደረጉና በእድሜም የገፉ በተለምዶ ሲኔር ሃኪሞች ተብለው የሚጠሩ ናቸው፡፡ ይህም በብዛት የህክምና ከፍሎች ሀላፊዎች፤ የህክምና ቦርድ አባል፤ የሲኔት አባልና በማህበረሰቡ በሚድያ እና በድርጅቶች ታዋቂ እንዲሆኑ ያስቻላቸው ናቸው፡፡
በብዛት በትላልቅ ሆስፒታሎች (በተለይ በጥቁር አንበሳና በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታሎች) ዉስጥ ትልልቅ ቦታዎችንና ሃላፊነትን የያዙና የመንግስት ሆስፒታሎችን ማህተም በቀላሉ ማግኘት የሚችሉ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ብዙ የግል ሆስፒታሎችም በብዛት ይሰራሉ፡፡
እነዚህ ሲኔር ማፊያ ዶክተሮች የሰዎች ዝውውር፤ የአካል ክፍል ብለታ (human organ harvesting and trading) እና ሌሎች ግልጽ የሕክምና ማጭበርበሮችን ያካሂዳሉ፡፡ በዚህ ስራም ጠቀም ያለ ገንዘብ በሀገር ዉስጥና በውጭ በሚገኙ ደላሎቻቸው በኩል ያፍሳሉ፡፡ የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በሁለት መንገድ ያሳልጣሉ፡፡
ለምሳሌ በአንድ ሰው ከመቶ ሺህ ብር በላይ በሆነ ክፍያ ለጤነኛ ሰው የሐሰት የውጭ ሕክምና ሪፈራል ሰነድ ያዘጋጃሉ፡፡ በሀገራቸው ተስፋ ለቆረጡና መሰደድ ለሚፈልጉ ወጣቶችን የሐሰት የውጭ የሕክምና ሪፈራል ወረቀቶችን ያዘጋጃሉ። እነዚህ ሰነዶች፣ ከደላሎችና በኢትዮጵያ ከሚገኙ የውጭ ኤምባሲዎች (እንደ ቱርክ፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች፣ ታይላንድ) ጋር በመተባበር ተዘጋጅተው በማታለል ቪዛ ያስገኛሉ።
ሀገር ውስጥ ተስፋ የቆረጡ ሥራ አጥ ወጣቶች፣ የውጭ ሀገር የተሻለ ኑሮን ተስፋ በማድረግ ወደዚህ ተግባር ይሳባሉ፡፡ ነገር ግን ከኢትዮጵያ ከወጡ በኋላ የተጎጂ ግለሰቦች ዕጣ ፈንታ ብዙውን ጊዜ አሳዛኝ ነው። የአንዳንዶቹ ዕጣ ፈንታ የማይታወቅ ሲሆን፣ በሕይወት መኖራቸውም እንኳ አይታወቅም። ለጤነኛ ሰዎች የኩላሊት፤ የአጥንት፤ የጉብት፤ የጭንቅላት ወዘተ ችግር እንዳለባቸው የውሸት ማስረጃ በመስጠት ያስለምናሉ፡፡
መንገድ ላይ፤ አደባባይ ላይና በሚኒ ባስ የሚያስለምኑና ከተለመነዉ ገቢ በደላሎቻቸው አማካይነት የሚካፈሉም አሉ፡፡ ጉዳዩ በዚህ አያበቃም። እነዚህ ሲኔር ማፊያ ዶክተሮች ሚስኪንና ድሃ ሰዎችን በደላሎቻችዉ በመመልመል፤ በሐሰት የውጭ ሕክምና ሽፋን ለአካል ሽያጭና ብለታ ያዘጋጃሉም፡፡ በድህነትና ተስፋ በመቁረጥ የተነሳ ወጣቶቹ ጉዳዩን አዉቀውና ተስማምተዉ ይገባሉ። በሐሰት ሪፈራሎች ወደ ውጭ ክሊኒኮች ይዘዋወራሉ፡፡
እዚያም የሰውነት ክፍሎቻቸውን ለገንዘብ ይሸጣሉ። ወደ ኢትዮጵያ በጎዶሎ አካል ሲመለሱ ከ150 ሽህ እስከ 300 ሽህ ብር ለሸጡት አካል በላኪው ሃኪምና ደላላ በኩል ይሰጣቸዋል፡፡ ይህ መጠን እነዚህ ማፍያ ሃኪሞችና ደላሎቻቸው ከሚያገኙት አንጻር በጣም ትንሽ ነው፡፡
አንዳንዶቹ በዚህ የተሰማሩ ማፍያ ሃኪሞች በወር ከ8 ሚሊዮን ብር ያላንሰ ስለሚያገኙ፡፡ ይህ የተደራጀ ወንጀል በትልልቆቹ የመንግስት ሆስፒታሎች ውስጠኛ ሰዎችና በደላሎች የጥፋት ትስስር የሚካሄድ ነው፡ ጋንጎቹ እስከ ኢምባሲ ሊንክ አላቸዉ፡፡
የውሸት ማስረጃ የሚሰጣቸው ሰዎች በደላሎች በኩል ከመቶ ሺህ በላይ የሆነ ገንዘብ ከከፈሉ በኋላ በመንግስት ሆስፒታሎች (በተለይ በጥቁር አንበሳና በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታሎች) ዉስጥ ካርድ እና ሌሎች ሰነዶች ይዘጋጅላቸዋል፡፡ ማፍያ ሃኪሞቹ የመንግስት ሆስፒታሎችን ኢሜይል፤ ሪፈራል ፎርምና ማህተም ይጠቀማሉ፡፡
የተቋሞቹን ኢሜይል በመጠቀም ወደ ኢምባሲዎች ሪፖርት ይጽፋሉ፡፡ በሐኪሞቹ ተቋማዊ ኢሜይሎች የተላኩ የሪፖርት ኢሜይሎች በኤምባሲዎች ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡ ግለሰቦች የቪዛ ጥያቄ ባቀረቡበት ኤምባሲ የቀረበውን የህክምና ሪፈራል ሰነድ ለመፈተሽ እንደማረጋገጫ ያገለግላሉ።
እነዚህ ማፍያዎች ሕዝቡን የሚዘርፉበትና የሚበዘብዙበት ሌላም መንገድ አለ። ብዙዎቹ በግል ሆስፒታሎችና ክሊኒኮች ይሰራሉ፡፡ በግል ክሊኒኮቻቸው የበለጠ ገንዘብ ለማስከፈል አላስፈላጊ ምርመራና ሕክምና ያካሂዳሉ።
በአዲስ አበባ የሰርጀሪ ማዋለድን (CS delivery) መጨመርን እንደ ምሳሌ እንውሰድ፡፡ በአዲስ አበባ በሰርጀሪ የማዋለድ የክፍያ መጠን በአለም ከፍተኛ ከሚባሉት አንዱ ነው። አንዳንድ ሐኪሞች ሴቶች ተፈጥሮአዊ ምጥና ወሊድ እንድኖራቸው ከመፍቀድ ይልቅ በሰርጀሪ እንዲወልዱ ይገፋፋሉ፡፡
ምክንያቱ የገንዘብ ፍላጎት ነው፡፡ በሰርጀሪ ማዋልድ ከተለመደው በምጥ ማዋልድ ከ6 እስከ 10 እጥፍ የሚበልጥ ገቢ ስላለው። ይህ ከታካሚ ደህንነት ጋር አይዛመድም፡፡ ሙሉ በሙሉ ከስግብግብነት የመነጨ ሲሆን ተፈጥሮአዊ ሂደትን ወደ ትርፋማ የቀዶ ጥገና ኢንዱስትሪ ይለውጣል። አለበለዚያማ በህክምና ሳይንሱ የሚመከረውና ለናትም ለልጅም የሚሻለዉ በምጥ መዉለድ ነዉ፡፡
የዚህ ማታለያ ሰለባዎች ብዙውን ጊዜ በኢኮኖሚያቸው የተሻሉ፤ በውጭ ድርጅቶቸ የሚሰሩ፤ ኢንሹራንስ ያላቸው፤ እና ደህና ገንዘብ መክፈል የሚችሉ እናቶች ናቸው። ተመሳሳይ ስግብግብነትም በላብራቶሪና ምርመራም ይስተዋላል። ታካሚዎች አላስፈላጊ የሆኑ ምርመራዎች ይታዘዙላቸዋለ፡፡ ለምሳሌ የደም፤ የሽንት፤ የሰገራና ራድዮሎጅ ምርመራዎች፡፡
ዋናው ምክንያት የጤና ሁኔታቸው የሚጠይቅ ስለሆነ ሳይሆን፣ እያንዳንዱ ምርምራ ለክሊኒኩ ገቢ ወይም ወደ የምርመራ ማእከላት ለአዘዘው ሐኪም ኮሚሽን ስለሚያስገኝ ነው። ለምሳሌ አንድ በአዲስ አበባ የሚገኝ የግል የራድዮሎጅ ማእክል MRI, US, X-ray, CT Scan, ECG, EKG etc ከመንግስት ሆስፒታሎች ለሚያዙ ሃኪሞች ጠቅም ያለ ኮሚሽን ይሰጣል፤ በዉድ ሆቴሎች ይጋብዛል፤ ያዝናናል፡፡
አንዳንድ መደለያ ስፖንሰሮች ያረጋል፡፡ ኮሚሽን ለማግኘት ሲባል የመንግስት ሆስፒታሎች የደም፤ የሽንት፤ የሰገራና ራድዮሎጅ ምርመራዎች እንዲቆሙ ሁሉ ይደረጋል፡፡ ይህ የድሃ ኢትዮጵያውያን ገንዘብ ያሟጥጣል፣ ሥቃያቸውን ይጨምራል፡፡ የማፊያ ሃኪሞቹን ኪስ ግን ያዳብራል፡፡
እንደ አጭበርባሪ ፓስተሮቹ እነዚህ የሕክምና ማፍያዎችም ሀፍረተ ቢስና ህሊ ቢስ ናቸው፡፡ ሀፍረተ ቢስና ትዕቢታቸው እንደ ስግብግብነታቸው ወሰን የለውም። ጎብለል ብለው በየሚዲያው እንዴ ሞዴል ዶክተርና ሰዉ ይቀርባሉ። በተማሪዎችና በበሽተኞች ጎበዝ መስለው ለመታየት ድራማ ይሰራሉ፡፡ ልክ እንደ ደላላ ሁሉንም እንደ ሁኔታው ያጫዉታሉ፡፡
በብዙ መገናኛ ብዙሃን “ሞዴል ሐኪሞች” ወይም “ልዩ ባለሙያዎች” ሆነው በእንግድነት ይቀርባሉ፡፡ ነገር ግን በስተጀርባ የነውር ጌቶች ናቸው፡፡ በወንጀልና ወራዳ የደላላ ተግባር የከበሩ፤ ለስም ሲኔር የተባሉ፤ በተግባርና በድብቅ ግን የነውር ጌቶች የሆኑ ናቸው፡፡ በዕድሜ ትልልቅ ግን በሞራል ትንንሾች ናቸው።
በቅርብ ለማያቁዋቸው የተከበሩ ግን በቅርብ ለሚያቁቸው “የነቀዙ ሾላካና አደቤዎች” ናቸው፡፡ የነሱን የሀብት መጠንና ስራ ላየ ባይበላ ቢቀርስ ያስብላል፡፡ ዘመኑ የተበላሸ እና የነውረኞች ነውና ህዝቡም ያደንቃቸዋል፤ ያሞግሳቸዋል፡፡ ሙያዊ በሆነ መንገድ የሚሰራው አብዛኛው ባለሙያ ግን ይደህያል፤ በህዝቡም ይረክሳል፡፡
እነ ነውር አይፈሪ አደቤዎች ግን ይህን ህዝብ አድብተዉ አካሉን ይበልቱታል፤ እነዴ እቃ ለፈረንጅ ያሻሽጡታል፤ ይሸቅሉበታል፡፡ እንድህ ነው የኢትዮጵያ የሞራል ዉደቀት፡፡ በሃቅ የሚሰራ ይደኸያል፤ ይራከሳል፤ ፋራ ይባላል፡፡ እሱ እራሱን ቢያገኘዉ የማይምረዉን አረመኔ ጋንግ ያደንቃል፡፡
ለማንኛውም መንግሥት፣ መገናኛ ብዙሃን፣ እና እያንዳንዱ ዜጋ የእነዚህን ሲኔር ማፊያ ዶክቶሮችን ወንጀሎች፤ ውስብስብ አውታሮችን፣ በአዲስ አበባ ያሉ የኤምባሲ ግንኙነቶችን፣ እና በግል ክሊኒኮች ውስጥ የተስፉፉ ሥነ ምግባር የጎደላቸው የህክምና ተግባራትን በተመለከተ ጥልቅ ምርመራ ሊያደርጉ ይገባል። እነዚህም ወንጀለኞችም ለፍትሕ ቢቀርቡ ለሁሉም መልካም የሚሆን ይመስለኛል።
ካልሆነ ግን ጉዳዩ ገንዘብ አለዉና የብዝበዛ ጌቶች ጉዳይ እየሰፋ የሚሄድ ነዉ፡፡
* ጸሐፊው በአዲስ አበባ በሚገኝ የመንግስትና የግል ሆስፒታሎች የሚሰራ ሃኪም ነው።
*መሠረት ሚድያ ላይ የሚቀርቡ አስተያየቶች በሙሉ የፀሀፊዎቹ እንጂ የሚድያው አቋም እንዳልሆኑ ልናስታውስ እንወዳለን።
መረጃን ከመሠረት!