በሽብር ተከሶ በእስር ላይ የሚገኘው የረ/ፕሮፌሰር ዳኜ አበበ ሶስተኛ መፅሀፍ ለንባብ በቃ
(መሠረት ሚድያ)- የሕሊና እስረኛው ረ/ፕሮፌሰር ዳኜ አበበ 'የኢትዮጵያ ቴአትር ጅማሬ እና ዕድገት' በሚል የፃፈው መፅሀፍ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕረስ መታተሙ ታውቋል።
ዩኒቨርስቲው በየዓመቱ ያሳተማቸውን መፅሐፍት ለአውደ ርዕይ እና ሽያጭ የሚያቀርብ ሲሆን ዘንድሮ ለ17ኛ ግዜ በተካሄደው አውደ ርዕይ የረዳት ፕሮፌሰር ዳኜን መፅሐፍ አሳትሞ ለንባብ አቅርቧል።
376 ገፆች ያሉት መፅሀፍ በውስጡ ስለ ኪነጥበብ እና ዘርፈ ብዙ ክዋኔዎች፣ ሂስ፣ ስነ ፅሁፍ፣ የቴያትር ምንነት በተለይም የኢትዮጵያ ቴያትር ጅማሮ እና እድገቱን በስፋት ያስቃኛል። ይህ መፅሐፍ ለተመራማሪዎች፣ ለተማሪዎች፣ ለሙያው ባለቤቶች እና በአጠቃላይ ለኪነጥበብ ቤተሰቦች እና ለማንኛውም አንባቢ አማራጭ በሚሆን መንገድ ቀርቧል።
ረ/ፕሮፌሰር ዳኜ ለእስር እስከተዳረገበት መጋቢት 10/2016 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቴአትሪካል አርት ዲፓርትመንት በመምህርነት ሲያገለግል የቆየ ሲሆን በተጨማሪም የተለያዩ ጥናትና ምርምሮችን ለዩኒቨርስቲው አበርክቷል።
ረ/ፕሮፌሰር ዳኜ እንደ ሌሎቹ የስራ እና የእስር ጓደኞቹ ለእስር ተዳርጎ የሽብር ክስ ተመስርቶበት የክስ ሂደቱን በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት እየተከታተለ እንደሚገኝ ይታወቃል።
መፅሀፉን በመግዛት ግለሰቡን እንዲያበረታቱ ወዳጅ ጓደኞቹ በመሠረት ሚድያ በኩል ጥሪ አቅርበዋል።
መረጃን ከመሠረት!