ዛሬ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ገደብጌ ከተማ የተከሰተው ምንድን ነው?
(መሠረት ሚድያ)- ዛሬ ምሽቱን ሚድያችን ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን፣ ወገራ ወረዳ የገደብጌ ከተማ ነዋሪዎች በርካታ መልዕክቶች ሲደርሱት አምሽቷል።
መልዕክቶቹ በአካባቢው መጠነ ሰፊ የሰው ህይወት መጥፋት እንደሆነ ይጠቁማሉ።
መሠረት ሚድያ እነዚህን ጥቆማዎች በመያዝ ባደረገው ማጣራት ቀደም ብሎ የፋኖ ሀይሎች በአካባቢው ባሉ የመንግስት ወታደሮች ላይ ጥቃት ከፈፀሙ በኋላ በምላሹ ወታደሮች ዛሬ ማምሻውን የከተማው ነዋሪ ላይ ጥቃት እያደረሱ መሆኑ ታውቋል።
እስካሁን ከሆስፒታል ምንጮች እና ከገደብጌ ከተማ ነዋሪዎች የደረሰን መረጃ እንደሚጠቁመው አብዛኞቹ እድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ የሆኑ 9 ሰዎች ዛሬ ማምሻውን በከተማው ተገድለዋል።
"ከፋኖ ጋር ምንም ንክኪ የሌላቸው የ80 ዓመት ሽማግሌን ጨምሮ አምስት ሰዎች አንድ ቦታ ላይ ተገድለዋል፣ ከቤታቸው እየተጎተቱ ወጥተው ተረሽነዋል" በማለት አንድ የከተማው ነዋሪ ተናግረው ተጨማሪ ነዋሪዎች በሌሎች የከተማው አካባቢዎች እንደተገደሉ ጠቁመዋል።
"አሁንም ሰው መግቢያ አጥቷል፣ እባካችሁ አግዙን። ፋኖ ገብቶ መከላከያን መትቶ ወጣ፣ ወታደሮች ደግሞ ንፁህ ሰውን ከቤት እያስወጡ መቱት" በማለት ሌላ የከተማው ነዋሪ ተናግረዋል።
አንድ የጎንደር ሪፈራል ሆስፒታል ባልደረባ ከ15 ያላነሱ በፅኑ የቆሰሉ ሰዎች ማምሻውን እንደመጡ አረጋግጠው ተጨማሪ ቁስለኞች እየመጡ መሆናቸው እንደተነገራቸው አስታውቀዋል።
በዚህ ዙርያ እስካሁን ከአማራ ክልል፣ ከፌደራል መንግስት እንዲሁም ከመከላከያ የተሰጠ መግለጫ የለም።
መሠረት ሚድያ!