የኢትዮጵያ አየር መንገድ 'የአሺዬሽን ኢንደስትሪ ኦስካር' በመባል በሚጠራው ትልቁ ሽልማት የአፍሪካ ምርጡ አየር መንገድ ተብሎ ተሸለመ
(መሠረት ሚድያ)- በፈረንሳይ እየተካሄደ ባለው የፓሪስ የአየር ትርኢት (Paris Air Show) ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ 'የአሺዬሽን ኢንደስትሪ ኦስካር' በመባል የሚጠራውን ትልቅ አለም አቀፍ ሽልማት ከአፍሪካ አሸናፊ ሆኗል።
መንገደኞች በሚሰጡት አስተያየት ላይ ተመርኩዞ በሚሰጠው ይህ 'SKYTRAX' ሽልማት ላይ አየር መንገዱ ምርጥ የአፍሪካ አየር መንገድ፣ ምርጥ የአፍሪካ የኢኮኖሚ ክላስ፣ ምርጥ የአፍሪካ ቢዝነስ ክላስ እና ምርጥ የአፍሪካ የበረራ አገልግሎት በሚሉ ዘርፎች አሸናፊ መሆኑ ታውቋል።
ድርጅቱ የአፍሪካ ምርጡ አየር መንገድ ተብሎ ሲመረጥ ዘንድሮ ለተከታታይ 8ኛ ግዜው ነው።
አሁን ላይ የበረራ መዳረሻዎቹ 140 የደረሱት አየር መንገዱ ለዚህ ሽልማት መብቃቱን አስመልክቶ ዋና ስራ አስፈፃሚው አቶ መስፍን ጣሰው በሰጡት አስተያየት ሽልማቱ የተቋሙን ሰራተኞች ጠንካራነት እና የደንበኞቹን ተአማኒነት ማግኘት ያመለክታል ብለዋል።
መሠረት ሚድያ እንደተመለከተው በዚህ ሽልማት ላይ የኳታር አየር መንገድ የአለማችን ምርጡ አየር መንገድ ሆኖ ሲመረጥ የሲንጋፖር አየር መንገድ፣ ካቴይ ፓሲፊክ አየር መንገድ፣ ኤምሬትስ እና ኦል ኒፖን የጃፓን አየር መንገድ እስከ አምስት ያለውን ደረጃ ይዘዋል።
በዚህ የአለም ዙርያ ዝርዝር ላይ አየር መንገዱ 38ኛ ደረጃን ይዟል፣ ይሁንና አምና ከነበረበት የ35ኛ ደረጃ በሶስት ደረጃ ዝቅ ብሏል።
መረጃን ከመሠረት!