ወንጀል መርማሪ ከግድያ ውጭ በማንኛውም መልኩ መመርመር እንዲችል የሚፈቅደው ህግ ከፀደቀ ከ20 ቀን በኋላ ማሻሻያ ተደረገበት
(መሠረት ሚድያ)- የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኔ 10/2017 ዓ/ም 'በወንጀል የተገኘ ንብረትን ሕጋዊ ማስመሰልና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከል' በሚል የወጣ አዋጅን ማፅደቁ ይታወሳል።
በዚህ አዋጅ ላይ በወንጀል ምርመራ ሂደት መርማሪው ሕይወቱን አደጋ ላይ ሲያገኝ፣ ነፍስ ከማጥፋት በስተቀር ራሱን የመከላከል ማንኛውንም እርምጃ መውሰድ እንደሚችል ተደንግጎ ነበር።
በርካታ ተቃውሞ ያስተናገደው ይህ የአዋጅ 1387/2017 አንቀጽ 26 መርማሪዎች የፈለጉትን ወንጀል በተጠርጣሪዎች ላይ እንዲፈፅሙ በር ይከፍታል በሚል ትችት ሲቀርብበት ነበር።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 3ኛ ልዩ ጉባኤውን ዛሬ ባካሄደው ስብሰባ ግን ይህንኑ አስፈላጊ ነው ተብሎ በበርካታ የምክር ቤት አባላት ሲሞገስ የነበረ ህግ ላይ 'ማሻሻያ' ማረጉ ታውቋል።
"ይህ ድንጋጌ እንዲታረም የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በዛሬው ዕለት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሳኔ ሀሳብ አዘጋጅቶ አቅርቧል" ያለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በውሳኔ ሀሳቡ ላይ ከተወያዩበት በኋላ ድንጋጌው ማሻሻያ ተደርጎበት የውሳኔ ሃሳብ ቁጥር 11/2017 ሆኖ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል ብሏል።
ይሁንና አስገራሚ በሆነ መልኩ የፀደቀው አዲስ አዋጅ ምን በሚል ድንጋጌ እንደተተካ ምክር ቤቱ አልገለፀም።
በርካታ ግለሰቦች፣ ተቋማት እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ህጉ ማሰቃየትን (torture) ጨምሮ ግፎች በዜጎች ላይ እንዲፈፀም በር ይከፍታል ብለው ሲሞግቱ ነበር።
አዋጁ በሽብርተኝነት ላይ የተሰማሩ ኃይሎችን ለመከላከል የተዘጋጀ ነው የሚል ሽፋን ቢሰጠውም በውስጡ ግን ፖለቲከኞችን፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን፣ ባለሀብቶችን፣ ጋዜጠኞችንና ታዋቂ ሰዎችን መብት የሚገድብ መሆኑን የፓርላማ አባሉ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ተናግረው ነበር።
ሕግ ሲወጣ ተፈጻሚ የሚሆነው ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ መሆን ሲገባው፣ ወደኋላ አሥር ዓመት ሄዶ ተግባራዊ ለማድረግ መሞከር አግባብ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡
መረጃን ከመሠረት!