የሸገር ከተማ አስተዳደር ለሚያስገነባቸው የዞን ፅህፈት ቤቶች እድሮች እያንዳንዳቸው 10 ሺህ ብር እንዲያዋጡ በደብዳቤ አዘዘ
(መሠረት ሚድያ)- የመንግስት ተቋማት የራሳቸውን ህንፃ ገንብተው፣ መሰረተ ልማት አሟልተው እና የሰራተኛ ደሞዝ ከፍለው ካበቁ በኋላ በአካባቢያቸው ለሚገኙ ህብረተሰብ ተኮር ተቋማት ደግሞ ከተረፋቸው ሲያጋሩ በብዛት ይስተዋላል።
ይህ የተለመደ አሰራር ግን በቅርብ ግዜ በብዙ የኢትዮጵያ አካባቢዎች እየተለወጠ ይገኛል፣ በዚህም የመንግስት ተቋማት መልሰው የሚያገለግሉትን ህዝብ እንደ ዞን ፅህፈት ቤት እና የገዢ ፓርቲ መሰብሰብያ አዳራሽ ብር አዋጥታችሁ ሲሉ ይታያል።
ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ትናንት ግንቦት 10/2017 ዓ/ም በሸገር ከተማ አስተዳደር ስር በሚገኘው የኮዬ ፈጬ ክፍለ ከተማ የቀርሳ ገተኑ ዞን የተፃፈ ደብዳቤ ነው።
የዞኑ ሰብሳቢ አቶ የሺጥላ ክፍሌ በስፍራው ለሚገኙ በርካታ እድሮች በፃፉት ደብዳቤ የዞኑ ፅህፈት ቤት ህንፃ ግንባታ በገንዘብ እጥረት መጓተት ስላጋጠመው እድሮች በነፍስ ወከፍ 10 ሺህ ብር እንዲያዋጡ አሳስበዋል።
"ሁሉንም የእድር ማህበራት በእኔነት ስሜት ለዚሁ ግንባታ እንዲያዋጡ በማድረግ ስለሆነ የእኛም ዞን በስሩ ያሉት የእድር ማህበራት አስር ሺህ ብር እንዲከፍሉ ወስነናል" የሚለው ደብዳቤው ክፍያው እስከ ሰኔ 13/2017 ዓ/ም እንዲከፈል አሳስቧል።
መረጃውን ለመሠረት ሚድያ ያደረሱት የአካባቢው ነዋሪዎች ቤታቸውን በግዴታ ቀለም ቀቡ፣ አዲስ አጥር እጠሩ እና አሮጌ ግንባታ አፍርሱ ሲባሉ ቆይተው አሁን ደግሞ ለክፉ ግዜ ብለው ያቋቋሙት እድር ጋር መምጣታቸው እንዳስገረማቸው ተናግረዋል።
"የኮሪደር ልማት ተብሎ ያ ሁሉ ገንዘብ ሲፈስ አይተናል። ለምን የመንግስት ህንፃቸውንም ራሳቸው አይሰሩም? በመዋጮ እና በኑሮ ውድነት የደቀቀውን ህዝብ በዚህ መልኩ ይበልጥ መቀጥቀጥ ምን ማለት ነው?" በማለት ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።
ከሸገር ከተማ በተጨማሪ እንደ ሲዳማ እና አፋር ባሉ ክልሎችም የብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ግንባታ ማስጨረሻ በሚል ህብረተሰቡ ገንዘብ በግድ እንዲያዋጣ እየተደረገ መሆኑን ከዚህ በፊት መዘገባችን ይታወሳል።
መረጃን ከመሠረት!