የዘንድሮው የ 'ግራንድ አፍሪካ ረን' እና የ 'አፍሪካ ኢምፓክት አዋርድ' በጥቅምት ወር በዋሽንግተን ዲሲ እንደሚካሄድ ይፋ ተደረገ
(መሠረት ሚድያ)- በአሜሪካን ሀገር በየአመቱ የሚካሄደው የግራንድ አፍሪካ ረን እና የአፍሪካ ኢምፓክት አዋርድ ዘንድሮ ለሰባተኛ ግዜ በዋሽንግተን ዲሲ ጥቅምት ወር ላይ እንደሚካሄድ ዛሬ ይፋ ተደርጓል።
በኖቫ ኮኔክሽን በየአመቱ የሚካሄደው እና ዘመናዊ መኪና የሚያሸልመው የግራንድ አፍሪካን ረን የአምስት ኪ/ሜ ውድድር በሺዎች የሚቆጠሩ የዲያስፖራው ማህበረሰብ አባላት በየዓመቱ የሚሳተፉበት ክስተት ሆኗል።
ዛሬ በአዲስ አበባ ስካይላይት ሆቴል በነበረ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ይፋ እንደተደረገው ሩጫው በመጪው 2018 ዓ/ም ጥቅምት 1 ቀን፣ ለታዋቂ ግለሰቦች እውቅና የሚሰጥበት የሽልማት ፕሮግራም ደግሞ ጥቅምት 2 ቀን ይካሄዳል።
ለሩጫ ውድድሩ የኦንላይን ምዝገባ ከወዲሁ መጀመሩ ዛሬ የተነገረ ሲሆን በአሜሪካ የሚገኙ ተሳታፊዎች በኖቫ ኮኔሽን ድረ-ገፅ (www.africanrun.com) አማካኝነት መመዝገብ እንደሚችሉ ተጠቅሷል።
ኖቫ ኮኔክሽን ዋሽንግተን ዲሲ መቀመጫውን ያደረገ ተቋም ሲሆን የሩጫ ውድድሩን እና የእውቅና ሽልማቱን ከመስጠትም ባለፈ ለኢትዮጵያውያን፣ አለፍ ብሎም ለአፍሪካውያን መሰባሰቢያ እና መተዋወቂያ ፕሮግራም አዘጋጅ ተቋም ሆኖ ቀጥሏል።
ዶ/ር ጋሻው አብዛ
የኖቫ ኮኔክሽን ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዶ/ር ጋሻው አብዛ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተቋማቸው በነዚህ ሁለት ፕሮግራሞች የዲያስፖራ ማህበረሰቡን ማገልገል በመቻሉ ትልቅ ክብር እንደተሰማቸው ገልፀዋል።
የዘንድሮውን የሩጫ እና የሽልማት ፕሮግራም አሌክሳንድሪያ ቶዮታ፣ ዳሸን ባንክ፣ የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን፣ ሮሚንግ ሩስተር፣ ጎፈሬ ስፖርትስ፣ አሪፍ ፔይ እና ጊፍት ሪል እስቴት ስፖንሰር አድራጊ ድርጅቶች መሆናቸው ታውቋል።
ሁለቱ ፕሮግራሞች ባለፉት አመታት እንደ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ፣ ደራርቱ ቱሉ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ ስለሺ ስህን፣ ገንዘቤ ዲባባ ላሉ ብርቅ የኢትዮጵያ አትሌቶች እውቅና ሰጥቷል።
ከዚህም በተጨማሪ እንደ ዝነኛው አርቲስት ኤኮን፣ ጋዜጠኛ መአዛ ብሩ፣ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)፣ አቶ ግርማ ዋቄ፣ አርቲስት ሙላቱ አስታጥቄ እና አርቲስት አስቴር አወቀ ላሉ ታዋቂ ግለሰቦች እውቅና ሰጥቷል።
ጥቅምት 1 በሚካሄደው ዝግጅት ላይ ከሚካፈሉ ተሳታፊዎች መካከል እድለኛ የሆነ ባለዕጣ የ2025 ቶዮታ ኮሮላ መኪና በዝግጅቱ ማጠናቀቂያ ላይ የዕጣ ማውጣት ስነስርዓት ተከናውኖ እንደሚሸለም ታውቋል።
የመኪና ሽልማቱ በአሌክሳንድሪያ ቶዮታ እንደሚቀርብ መሠረት ሚድያ የደረሰው መረጃ የሚጠቁም ሲሆን ታላላቅ አትሌቶች እና የኪነጥበብ ባለሞያዎች በክብር እንግድነት እንደሚሳተፉም አዘጋጁ ኖቫ ኮኔክሽንስ የላከው ጋዜጣዊ መግለጫ ይጠቁማል።
መረጃን ከመሠረት!