በተስፋዬ ወ/ዮሐንስ ሀይሌ ለመሠረት ሚድያ
(መሠረት ሚድያ)- በሚዛናዊ የሚዲያ ስራዎቹ የምናውቀው የኢትዮጵያ ኢንሳይደር መስራችና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ ከአንድ ሳምንት እስር፥ ሶስት ዋስትና እና የዋስትና ሳምንት መንገላታት በኋላ መፈታቱ ስቅላት ውስጥ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ሚዲያ ሰሞነኛ አበይት ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ነበር።
በሌላ በኩል በሎሌነት መንግስቴን አትንኩብኝና አንገታችሁን በካራ የሚሉ አድርባዮች በማን አለብኝነት በግብር ከፋይ ህዝብ ገንዘብና ሀብት ሲፈነጩ፥ የጥላቻ ንግግር ሲያሰሙ፣ የህግ አካላት ፖሊስና አቃቤ ሀግ፥ ለጋዜጠኝነትና ለጋዜጠኛ መብት፥ ደህንንትና ክብር መጠበቅ ቆሜያለው የሚሉት ተቋማት ዝም ጭጭ ማለትን መርጠው ፍትህ ሆይ መገኛሽ ወደየት ይሆን? አስብሎኛል።
ጋዜጠኝነትና ተያያዥ የሆኑ ሙያዊ ጉዳዮች አንድም በራሱ በሴክተሩ ውስጥ በሚገኙ ባለሙያተኞች ምክንያት በሌላ በኩል ደግሞ መንግስት በሚያደርሳቸው ጫናዎችና ጣልቃ ገብነት ከመንግስትና ደጋፊዎቹ ወገን ካልተቆመ በስተቀር ሙያው ከአካላዊ ጥቃት፥ እስር እስከ ህይወት መስዋእትነት ድረስ እየወሰደ የሚገኝ አስፈሪ ዘርፍ ሆኗል።
ሚዛናዊ፣ ቅቡል፣ እውነተኛ የመረጃ ምንጭነት፣ ጥራት፥ ሙያተኛነት፣ የመረጃ ነፃነትና ተጠያቂነት የሚጠይቀው የጋዜጠኝነት ሙያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸረ፥ ለሙያዊ ጥበቃ ለመቆም አቅም እያጣ፥ ስልጣን ላይ ያለ ገዢ ፓርቲና የፖለቲከኛ መፈንጫ፥ መደስኮሪያ መሆን ከጀመረ ሰነባብቷል።
እውነት፥ ፍትህ፥ ተጠያቂነት በሙያው ውስጥ አይነኬ ርዕሰ ጉዳይ መሆንን መርጠዋል።
ከ130 በላይ የመንግስትና ንግድ ራዲዮና ቴሌቭዝን ጣቢያዎችና የህትመት ሚዲያ፥ ከ200 በላይ ኦን ላየን ሚዲያ፥ የመገናኛ ብዙሃንን ተደራሸነት ለማስፋት በርካታ የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤቶች ያቀፉ ዩኒቨርስቲዎች አገልግሎት ላይ የሚገኙ፥ ከ25 በላይ የሙያ ማህበራት በርካታ ሚዲያዎችንና የሚዲያ ባለሙያተኞችን አቅፈው አለን ቢሉም ቅሉ ጋዜጠኞች ከእስር፥ ከአካላዊ ጥቃት፥ ዛቻና ማስፈራሪያ ከእውነትና ፍትህ ጋር የመቆም ሙያዊ መርህ ጋር ተለያይተዋል።
ከግብር ከፋይ ከሚሰበሰብ ገንዘብ የሚተዳደሩት ከፖለቲካ አመራርና የመንግስት በጀት ያልተላቀቀው የመንግስት ሚዲያ፤ በተለይም ደግሞ በሀገሪቱ ውስጥ ባለፉት ስድስት ዓመታት የተከሰተውን ለውጥ ተገን በማድረግ በ"ነፃነት" ስም የፖለቲካ ትኩሳትን እየተከተሉ ማጦዝ የተለመደ ሆኗል፡፡
የተቆጣጣሪው አካል ወገንተኝነትና ቸልተኝነት ተጨምሮበት ለመመልከት የምንሻውን ዲሞክራሲያዊ ስርዓት የሚያቀጭጭ፣ ጥላቻን የሚሰብክ፣ የሐሳብ ልዩነትን የማያከብር፣ ቅጥ ባጣ ወገንተኝነት ታጅቦ በአቅምና ሙያዊ ስነምግባር ጥያቄዎች ውስጥ ባሉ ጋዜጠኛ ተብዬዎች መበራከት ታግዞ ሙያው እያደር ከጥያቄ ውስጥ ከመግባቱ ባሻገር የግለሰብና የቡድን መጠቀሚያ መሆንን መርጠዋል፡፡
ይህም ሀገሪቱ በምትከተለው የፖለቲካ ስሪትና የተቋማት ነፃነት ውስጥ ያልታደለው የጋዜጠኝነት ሙያ አጎብዳጅነት ፈተናውን ከባድ አድርጎታል፡፡
ምንጩ እስካሁን የመጣንበት መዋቅራዊ የሆነ የአስተሳሰብና የአደረጃጀት መንገድ መሆኑ እሙን ነው፡፡
ተቋማዊ ነፃነት አለመኖሩ ደግሞ የበለጠ የችግሩን ውስብስብነትና ተስፋ አስቆራጭነት በማባባስ የምንመኘውን ሙያዊ ልዕልና ለማምጣት ከፍ ያለ ትግል እንደሚያስፈልግ ያመለክታል፡፡ ሀገራችን ያላት የሶስት አስርት ዓመታት የመገኛኛ ብዙኃን ታሪክ ከጥቂቶች በስተቀር፤ በሀገሪቱ የፖለቲካ አመራር ጫና ስር የወደቀ፣ በተቃዋሚው የፖለቲካ አቀንቃኝ ዘዋሪነት ተወጥሮ የተያዘ፣ ሙያዊ ስነምግባርን በአገልጋይነትና አሽከርነት ያበላሸ ነው፡፡
በመሆኑም ጋዜጠኝነትን ከቀጥታ ቁጥጥር፣ ግፊትና ተፅእኖ ባሻገር አጎንብሶ መስራት የሙያዊ መገለጫው እስኪሆን ድረስ የካድሬ መፈንጫ አድርጎታል፡፡
ይህንን አመለካከት፤ በተለይም ከዚህ አምስት ዓመታት ወዲህ በሀገሪቱ ውስጥ ፖለቲካዊ ችግሮች በተከሰቱ ቁጥር ይበልጡኑ ፊት ለፊት እያገጠጠ ከተጠያቂነት እጅጉን ባፈነገጠ መልኩ እንድንለምደው ተገደናል፡፡
በለውጡ ሂደት ውስጥ ሚዲያው የነበረው ተነሳሽነት የሚዲያ ህግ ማሻሻያዎች፣ ሚዲያውን ለማሻሻል የተገቡ ቃሎች፣ በህግ አርቃቂው አካል ተሰርተውና ተጠናቀው ውሳኔ የሚጠብቁት አዋጆችና ደንቦች ሚዲያውን ተስፋ ሰንቆ የሚጠብቃቸው ውጤቶች የነበሩ ቢሆንም ቅሉ በብዙ ወደኋላ በሚመልሱ አንቀፆች ታጅቦ ከወራት በፊት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡
ይህም የአብዛኛው የመገኛና ብዙኃን አሰላላፍ በአሮጌ አቁማዳ ውስጥ ያለ አዲስ የወይን ጠጅ ዓይነት አንዲሆን አድርጎታል፡፡ ላለፉት ሶስት አስርት አመታት ለሚጠጋ ጊዜ ሲከተላቸው የነበሩት የተፅእኖ፣ የማፈን፣ የሌሎችን ድምፅ የመሰማት ችግሮችን ሲተገብሩ የነበሩ የሚዲያው ፈላጭ ቆራጭ አመራሮችና ጋዜጠኞች ያኔ የነበረውን መኮነንና ዛሬ ያለውን ፃዲቅ እድርጎ ማሳየት የእለት ተዕለት ጉዳያቸው ሆኗል፡፡
ዛሬም በጋዜጠኝነት ምክንያት ግድያ፣ እስር፣ ማፈን አሁን አሁን ደግሞ ምንም አንዳይዘግብና የጋዜጠኝነት ተግባራት እንዳያከናውን ማስፈራራት ደርሶባቸው ቤታቸው የተቀመጡና የተሰደዱ ቀላል የማይባሉ የሙያ አጋሮቻቸን ይገኛሉ፡፡
የጋዜጠኝነትና የፖለቲከኝነት ሚና ሲደበላለቅ እንዲሁም ከሚፈልጉት መልኩ ብቻ አቅጣጫዎቹን ሲያሲዙ ተመልክተናል፡፡ አንዳንድ ጋዜጠኞች ወግ አማረልኝ በማለት አብዛኛው ሰው በሚሰማው፣ በሚመለከተውና ከዚያም አልፎ በሚኖረው የእለት ተዕለት ህይወት ውስጥ፤ ውሃ በማይቋጥር አመክንዮ ላይ በመመሥረትና ፟ምሁራን ፟፟፟፟ና ፟፟፟፟አንዳንድ የከተማው ነዋሪዎች ፟፟፟፟ በሚል ታርጋ በማጀብ የሚያቀርቧቸው ትንታኔዎች እነርሱ ብቻ ሳይሆኑ አርታኢና ተቋሙም ጭምር ለሙያው ያላቸውን ንቀት፣ ለህዝቡ ያላቸውን ማን አለበኝነት የሚያሳዩ ይመስለኛል፡፡
ተፅህኖ የማያመጣው የሙያ ማህበራት ሚና ስንመለከት ድሕረ 2010 የኢትዮጵያ መገኛና ብዘሃን ሁኔታ ዳሰሳ የጥናት ሪፖርት እንደሚስረዳው 65 ከመቶ የሚሆኑ ጋዜጠኞች በጋዜጠኛ የሙያ ማህራት ውስጥ ለመሳተፍ ፍላጎት እንደሌላቸው አስታውቀዋል፡፡
ይሁን አንጂ 25 በጋዜጠኝነት ዙሪያ የሚሰሩ የሙያ ማህበራት በአሁኑ ጊዜ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ቁጥሮች ጀርባ የሚነግሩን በርካታ ጉዳዩች አሉ፡፡ የሙያና ብዙሃን ማህበራት በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 31 የተደነገገውን የዜጎች የመደራጀት መብት መሰረት በማድረግ የአባላትን መብትና ጥቅም በማስከበር፣ የአባላትን አቅም በማሳደግና ለሙያውና ለባለሙያተኛው ድምፅ፣ ውግንና ኖሯቸው የሚመሰረቱ ተቋማት ናቸው፡፡
በሀገራችን ረጅም እድሜ ያስቆጠሩ በርካታ የሙያ ማህበራት ይኑሩ እንጂ ተፅህኖ ፈጣሪነታቸው፣ የአባላት ቁጥራቸው ለአብዛኛዎቹ እዚህ ግባ የሚባል አይነት አይደለም፡፡ የጋዜጠኝነት ማህበራቱም ከዚህ ባህል መላቀቅ ያልቻሉ ናቸው፡፡
በማህበራቱ የአመሰራረት ሁኔታ፣ አደረጃጀትና መዋቅራቸው፣ በያዟቸው የስራ አመራር ኮሚቴ፣ የውሳኔ አሰጣጥ ሂደታቸው፣ ለሙያውና ለሙያተኛው በሚሰጡት ውግንና እና ድምፅ ልዩነቶች ምክንያት በአንድ ሙያ ውስጥ ጠንካራ ያልሆኑ፣ ተፅህኖ የማይፈጥሩ፣ በጥቂት ስራ አስፈፃሚዎች ትጋትና የኪስ ፋይናንስ ድጋፋ ከቢሮ ኪራይ ክፍያ ጀምሮ የሚያምጡ፣ የቁጥር ማህበራትን መመሰረት ተችሏል፡፡
እነዚህ ማህበራት አብዛኛዎቹ ቢሮአቸው እንኳ በቂ የሆነ የቢሮ መገልገያ ያልተሟሉላቸው፣ ቋሚ የፅህፈት ቤት ሰራተኛና ባለሙያ የሌላቸው፣ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ለማካሄድ እንኳን ወገቤን እጄን የሚሉ ናቸው፡፡
ከዚህም እልፍ ሲል የአንዳንዶቹ የጋዜጠኝነት ሙያ ማህበራት ሃላፊዎች ደግሞ ከዓመት እስከ ዓመታት የስልጣን ሽግሽግ የማይታይባቸው መሪ ግለሰቦች የሙያ ማህበራት መጠሪያ እስከመሆን የደረሱ ናቸው፡፡
እንደመፍትሄ ሙያውን፥ ሙያተኛውን፥ ፕሬስንና ተቋማቱን ነፃ ማውጣት
ያለ ነፃነትና መርህ የቆመ ሚዲያ ለሀገር፣ ለተቋሙም ሆነ ለሰራተኞቹ ከሚያስገኘው ትርፍ ይልቅ ኪሳራው የከፋ ነው፡፡ የተቋማቱ ነፃ መውጣት የሚጀምረው ከአስተሳሰብ፣ ከተቋማዊ አደረጃጀት ማስፈንና ከአመራሩ ቁርጠኝነት ነው፡፡
በአስተሳሰቡ የመጣውን ለውጥ ሙያዊ በሆነ ሁኔታ የመለየት፣ የመተንተንና አቅጣጫ የሚያሳይ ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት ግድ ይላቸዋል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን በአደረጃጀት እና ራሱን በፋይናንስ የሚችልበት ስልታዊ እቅድን መንደፍና አመራር መስጠት ይጠበቅበታል፡፡ የአመራሩ ቁርጠኝነት የተቋማቱን ለውጥ የበለጠ ያፋጥነዋል፡፡
ቁርጠኝነቱ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ተላቆ ፍትሃዊ፣ ተደራሽና ተአማኒ መረጃንና ፕሮግራምን ከማቅረብ ጎን ለጎን ለማህረሰብ ግንባታ የሚበጁ ሃሳቦችን አመንጭቶ በተግባር ላይ እስከማዋል ድረስ ይዘልቃል፡፡ የሚዲያ አመራርና ተቆጣጣሪነት ሚና ተዘንግቷል፡፡
የሚዲያው ተቆጣጣሪ አካል ልክ እንደሚዲያው ሁሉ ራሱን መልሶ መላልሶ ሊመለከት ግድ ይለዋል፡፡ ለሚዲያው እዚህ ደረጃ መድረስ አንድም ነፃነቱን የተነፈገ ተቋም ስለመሆኑ ማሳያ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ለደረሱት ጥፋቶች ሁሉ እኩል በሚባል ደረጃ ራሱን ተጠያቂ ማድረግ ይኖርበታል፡፡
በእነዚህ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ እያንዳንዳቸው የስራ ሃላፊዎች ከህዝቡና ከተቋማቱ አደረጃጀት የተሰጣቸውን ሃላፊነት በተወጡ ቁጥር፤ አዚች ሀገር ላይ ሚዲያን በሚመለከት ለሚደርስ ማንኛውም መልካም ስራ ተመስጋኝ፤ ሃላፊነታቸውን ባልተወጡ ቁጥር ደግሞ ተወቃሽነትና በህግ ተጠያቂነት ነገ ከነገ ወዲያ እንደሚመጣ መገንዘብ ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ፡፡
ይህም ካልሰራ አማራጭ ሚዲያዎችን መደገፍ፥ ማቋቋምና ማገዝ አይነተኛ መፍትሔ ነው። ለዚህ ይህ የመሠረት ሚዲያ ፕላትፎርም አይነተኛ ምሳሌ ነው። ዘመኑ በቴክኖሎጂ እየዘመነ የተሻሉ የመገኛኛ ዘዴዎችን እየተዋወቁ የሚገኝበት ጊዜ ነው።
ለእውነት፥ ለመረጃ፥ በሃላፊነትና በአግባቡ የሚሰሩ አማራጭ ሚዲያዎችን ስራቸውን በማበረታታት፥ ሚናቸው ተሻለ እንዲሆን፥ ተደራሽነታቸው እንዲፋጠን፥ ዘላቂነታቸውን ለማረጋገጥ በሚቻለው ሁሉ መደገፍ ሙያውን ነፃ ማውጣት፥ ህብረተሰቡ አስተማማኝ የመረጃ ምንጭ እንዲኖረው ማድረግ ያስችላል።
ተስፋዬ ወልደዮሐንስ ሃይሌ
ሲያትል፥ ዋሽንግተን tesfayewoldeyohanes.h@gmail.com
*መሠረት ሚድያ ላይ የሚቀርቡ አስተያየቶች በሙሉ የፀሀፊዎቹ እንጂ የሚድያው አቋም እንዳልሆኑ ልናስታውስ እንወዳለን።
መረጃን ከመሠረት!