በዳሶ ኡመር ለመሠረት ሚድያ
(መሠረት ሚድያ)- የዳኝነት ነፃነት በኢፌዴሪ ህገ መንግስት እውቅና የተሰጠው መሰረታዊ የፍትህ መርህ ነው፡፡ ዳኞች በህግ እና በህግ ብቻ እንዲሰሩ የዳኝነት ነፃነት እጅግ ወሳኝ ነው፡፡
የዳኝነት ነፃነት ጠቀሜታው በዋናነት ለህብረተሰቡ ሲሆን ይኸውም ዜጎች በህግ ተማምነው እንዲኖሩ እና በህግ የተሰጣቸው መብት ሲነካ በህግ ብቻ የሚዳኝ ነፃነቱ የተጠበቀ ፍርድ ቤት ቀርበው መብታቸውን ማስከበር የሚችሉ በመሆኑ ነው፡፡
አንድ ዳኛ ነፃ መሆን የሚገባው ከራሱ ስሜት እንዲሁም ከፍርድ ቤቱ አመራር፣ የስራ ባልደረባው እና ከሌሎች ማናቸውም የውጭ አካላት ጣልቃ ገብነት ነው፡፡ የዳኝነት ነፃነትን ማስከበር ለዳኛው ህጋዊ ግዴታው ሲሆን ይህን አለማስከበር ደግሞ ሙያዊ ግዴታን መጣስ ነው፡፡
ዜጎች በትኩረት ሊያውቁት የሚገባው ሀቅ የዳኝነት ነፃነት አስፈላጊነቱ ለግለሰብ ዳኛው ሳይሆን ለጠቅላላ ህብረተሰቡ መሆኑን ነው፡፡ ይህ መብትም የተቀመጠው የዳኝነት ተጠያቂነትን ባጣመረ መልኩ ነው፡፡
ዳኛ ነፃ ሆኖ በህግ እና በህግ ካልሰራ እንዲሁም ነፃነቱን በሚፈታተኑ የውጭ እና የውስጥ አካላት ላይ እርምጃ ካልወሰደ በህግ ተጠያቂነት ይኖርበታል፡፡ ከህዝቡ አደራ ለዳኛው የተሰጠው ትልቁ ኃላፊነት የዳኝነት ነፃነትን እንዲያስጠብቅ እና ራሱም ነፃ ሆኖ በህግ እና በህግ ብቻ እንዲሰራ ነው፡፡
የህግ መርሁ ይህ ቢሆንም በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ውስጥ የዳኝነት ነፃነትን በመጣስ ረገድ በየደረጃው ያሉ አንዳንድ የፍርድ ቤት አመራሮች ከፍተኛ አስተዋዕፆ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
ከፍርድ ቤት አመራሮች በተጨማሪ አንዳንድ የአስፈፃሚ አካላት አመራሮችም በዳኝነት ነፃነት ላይ ጣልቃ እየገቡ ይገኛሉ፡፡ በየደረጃው ያሉ አንዳንድ ዳኞችም የዳኝነት ነጻነትን ከማስከበር ይልቅ መርሁ እንዲጣስ የመተባበበር ሁኔታ እያሳዩ መሆኑ በፍትህ ስርዓቱ ላይ ስጋት ደቅኗል፡፡
የፍርድ ቤት ትዕዛዞች የማይከበሩበት ሁኔታ የተፈጠረውም የዳኝነት ነፃነትን በማክበር ረገድ ዳተኝነት በመኖሩ ሲሆን ህብረተሰቡም በፍርድ ቤቶች ላይ ያለው እምነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ የመጣው በዚሁ ምክንያት ነው፡፡
የፍትህ ስርዓቱ በተፈለገው መልኩ እንዳይሻሻል እንቅፋት የሆኑት በርካታ ምክንያቶች ያሉ ቢሆንም በዋናነት ግን የዳኝነት ነፃነት አለመከበር፣ ከፍተኛ የዳኝነት ጣልቃ ገብነት መኖር፣ በየፍርድ ቤቱ ጉዳይ እናስፈፅማለን የሚሉ የፍትህ ደላሎች መበራከታቸው፣ ጥብቅ የሆነ እና በማስረጃ ላይ የተመሰረተ የዳኝነት ተጠያቂነት አለመኖሩ፣ ከዳኞች ተጠያቂነት በዘለለ የፍርድ ቤት አመራሮች ተጠያቂነት አለመኖሩ፣ ፍትህን በገንዘብ የመግዛት አንዳንድ ዝንባሌዎች መኖራቸው፣ ብቃት ያለው ባለሙያ አለመኖሩ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
በአገሪቱ ውስጥ በየጊዜው የሚከሰቱ አለመረጋጋቶችን በመከተል በዜጎች ላይ እስር ሲፈፀም ክርክሩ የሚካሄደው በፖሊስ እና በተጠርጣሪ ሆኖ ይህን ክርክር የሚመራው ደግሞ ፍርድ ቤት በመሆኑ ሚዛናዊ ፍርድ ለመስጠት በችሎቱ የተሰየመው ዳኛ ነፃና ገለልተኛ ካልሆነ የሚቻል አይሆንም፡፡
የዳኝነት ነፃነት መኖሩ ጠቀሜታው ከህብረተሰቡም በላይ መንግስት በህዝቡ ዘንድ ቅቡልነት እንዲኖረው እና ጠንካራ የፍትህ ስርዓት የዘረጋ መሆኑ አንዱ ማሳያ ሆኖ የሚቀርብ ነው፡፡
በአንዳንድ የፌዴራል ፍርድ ቤት አመራሮች በኩል የሚፈፀመው ጣልቃ ገብነትም በስልክ እየደወሉ ዳኛው ጉዳይ እንዲፈፅም ትዕዛዝ መስጠት የማይፈፅም ከሆነ ደግሞ የዲሰፕሊን ክስ እንደሚቀርብበት ማስፈራራት፣ በተግባርም በማይታዘዙት ላይ ለክስ የሚሆን ጉዳይ በጥልቅ ፍተሻ እና ዘመቻ ተፈልጎ ክስ በማቅረብ ለሌሎች ማስተማሪያ ማድረግ፣ ዳኛው በስነ ልቦና እንዲዳከም ጉቦ መቀበልህ በቪዲዮ ተቀርፆ መጥቶልኛል የሚል ሀሰተኛ መረጃ እንዲነገረው በማድረግ ጣልቃ ገብነቱን የማመቻቸት ሁኔታ መኖሩ፣ ይህን ጉዳይ ካልፈፀምህ ሹመት አትሾምም የሚል ዛቻ መሰንዘር፣ የዳኝነት ሹመት ምልመላን በ2015 መጋቢት ወር በመጀመር እስከ አሁን ድረስ ባለማጠናቀቅ (ሁለት አመት ከ2 ወር ድረስ በማራዘም) በሹመት ምልመላው ውስጥ ያለፉትን በዚህ በማስፈራራት ጉዳይ እንዲፈፅሙ የማድረግ ስራ እተሰራ ይገኛል፡፡
“የአገሪቱ ልጆች በሙሉ የፍትህ ሰጭው አካል ልጆች ሆነው እያለ እንዴት የአንድ ግለሰብ ዳኛ ልጅ ማደግ አለማደግ ሊያሳስበው ይችላል የሚለው የሁላችንም ጥያቄ ነው”
በፍርድ ቤቱ ታሪክ የዳኛ ምልመላ ይህን ያህል ጊዜ ወስዶ የማያውቅ ሲሆን ይህ መራዘም ለአንዳንድ አመራሮች እንዲሁም ዳኛውን ተፅዕኖ ውስጥ ማስገባት ለሚፈልጉ ተከራካሪ ወገኖች ጠቀሜታው የጎላ ስለሆነ ነው፡፡ በተግባር ያለው ነገር ይህ በመሆኑ ድፍረት ኖሮት የዳኝነት ነፃነትን የሚያስከብር ዳኛ እየተመናመነ የመጣ ሲሆን ልጆቼን ላሳድግበት የሚለው አባባል መደበቂያ ሆኖ የፍትህ ስርዓቱን ክፉኛ እጎዳው ይገኛል፡፡
ልጄን ላሳድግበት የሚለው አባባል ሌሎች ሰዎች በፍትህ እጦት ምክንያት ልጆቻቸውን እንዳያሳድጉ ከተደረጉ ፍትህ መስጠት ያለበት አካል እንዴት ህሊናው ሊርፍ ይችላል፡፡
የአገሪቱ ልጆች በሙሉ የፍትህ ሰጭው አካል ልጆች ሆነው እያለ እንዴት የአንድ ግለሰብ ዳኛ ልጅ ማደግ አለማደግ ሊያሳስበው ይችላል የሚለው የሁላችንም ጥያቄ ነው፡፡
በአገሪቱ የፖለቲካ፣ የማህበራዊ፣ የኢኮኖሚያዊ እና የባህላዊ መስተጋብሮች ውስጥ በቆራጥነት የህዝብን እና የአገርን ጥቅም በማስቀደም ላለመስራት እንቅፋት የሆነው ነገር ልጄን ላሳድግበት የሚለው የተሳሳተ አባባል ነው፡፡
ስለሆነም በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ዘንድ በአንዳንድ የፍርድ ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች በኩል የሚደረገው የዳኝነት ጣልቃ ገብነት ካልቆመ የፍትህ ስርዓቱ አደጋ ውስጥ ስለሚገባ የሚመለከተው አካል አጣርቶ አስቸኳይ ማስተካከያ ሊያደርግበት ይገባል የሚል አስተያየት አለኝ፡፡
በዳሶ ዑመር
መሠረት ሚድያ፣ የህዝብ ድምፅ!